አዲሱ አፋኝ አዋጅ በወጣ ማግስት ዝርፊያ እየተጧጧፈ ነው

ጥቅምት ፯ (ሰባት) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- ከተለያዩ አካባቢዎች የሚደርሱን መረጃዎች እንደሚያሳዩት መላውን የአገሪቱን ህዝብ ለማፈን የወጣው አዋጅ ተግባራዊ ከሆነበት ቀን አንስቶ ፣ በእዙ ሰንሰለት ወይም ኮማንድ ፖስቱ ስር ነን ያሉ የተደራጁ የገዢው ፓርቲ አባላት በባለሃብቶች ቤት እየገቡ በማስፈራራት ዝርፊያ እየፈጸሙ ነው።

እነዚሁ ታጣቂዎች፣ የኮማንድ ፖስቱ አባላት ነን በማለት ባለሃብቶችን “ የተቃዋሚ ደጋፊዎች መሆናችሁን ደርሰንብታል፣ ገንዘብ ካመጣችሁ አንነካችሁም “ በመላት ገንዘብ መዝረፍ መጀመራቸውን ለደህንነታቸው በመስጋት ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ሰዎች ተናግረዋል።

ሰሞኑን ከተከናወኑት ዝርፊያዎች መካከል በአዲስ አበባ ኮልፌ ቀራኒዮ የተፈጸመው ከፍተኛ ነው። ቤቴል እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ፣ የኮማንድ ፖስቱ አባላት ነን ያሉ ግለሰቦች አቶ ኡስማን ከተባሉ ግለሰብ ቤት በመግባት 400 ሺ ብር እና የተለያዩ ጌጣጌጦችን፣ ሞባይል ስልኮችን ወስደዋል። ምሽትና ሌሊት አካባቢ የሚጓዙ ሰዎችን በማስቆም መታወቂያ አሳይ በማለት ኪስ እየበረበሩና ስልኮችን እየቀሙ እየተሰወሩ መሆኑን ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ተናግረዋል።