ታዋቂው የነጻነት አርበኛ አበራ ጎባው ዶጋው በረሃ ላይ ጥቃት ካደረሰ በሁዋላ ከጀርባ ተመትቶ መገደሉን የአይን እማኞች ገልጸዋል።

ጥቅምት ፬ (አራት) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- በዛሬው እለት በ9 ኦራል መኪኖች የተጫኑ ወታደሮች ዶጋው ገብተዋል። በከፍተኛ የቁጣ ስሜት ውስጥ የሚገኙት ወታደሮች ህዝቡ የኢሳት ስርጭቶችን እንዳይመለከት ለማድረግ በከተማዋ ያሉ ዲሾችን ሲነቃቅሉ ውለዋል።

ነዋሪዎች እንደገለጹት ትናንት የግለሰቦችን የጦር መሳሪያዎች ለማስፈታት እንዲሁም በአካባቢው የተደራጁ ሃይሎች አሉ በሚል ከጎንደር የተንቀሳቀሰው የመከላከያ ሰራዊት፣ ዶጋው በረሃ ላይ ሲደርስ  ከነጻነት ተዋጊዮች ተኩስ ተከፍቶበታል። ታዋቂው አርበኛ አበራ ጎባው የመከላከያ ነዳጅ የጫነን መኪና በጥይት መትቶ እንዲገለበጥና እንዲቃጠል ማድረጉን፣ በተከታታይ በነበሩ ፒክ አፕ መኪኖች ላይ እሱና ጓደኞቹ አከታትለው ጥቃት በመሰንዘር በርካታ ወታደሮችን ከገደሉ በሁዋላ፣ ከሁዋላ የነበሩ ወታደሮች በአልሞ መቺ የጦር መሳሪያ  መግደላቸውን የአይን እማኞች ተናግረዋል።

በአካባቢው ሲካሄድ በነበረው ተኩስ በርካታ ወታደሮች የተገደሉ ሲሆን፣ ይህን ተከትሎ የአካባቢው ወጣቶች አካባቢያቸውን ለቀው ጫካ ገብተዋል። አበራ ጎባውን በስርዓት ለመቅበር እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ እያሉ በጧት በርካታ ወታደሮችን የጫኑ 9 ኦራል መኪኖች የገቡ ሲሆን፣ ያገኙዋቸውን ሴቶች ከመደብደብ በተጨማሪ፣ በእየቤቱ የተተከሉ የሳተላይት ዲሾችን ሲነቃቅሉ አርፍደዋል።

ህወሃት/ኢህአዴግ መራሹ መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ካወጣ ጊዜ ጀምሮ በአማራ እና በኦሮምያ ክልሎች የሚገኙ የግለሰብ የጦር መሳሪያዎችን በመቀማት፣ ኢሳትንና ሌሎችም ከውጭ ሃገራት የሚተላለፉ የዜና ማሰራጫዎችን ወጣቶች በሞባይል ስልኮቻቸው እንዳይመለከቱ በማድረግ እንዲሁም የሳተላይት ዲሾችን በመንቀል፣ የተቃውሞ አስተባባሪ ናቸው ብሎ የሚፈርጃቸውን ሃይሎች በማሰር፣ በስራ ማቆም አድማ የሚሳተፉ ነጋዴዎችን በማፈን እና ሌሎችም እርምጃዎችን በመውሰድ በአገሪቱ የተቀጣጠለውን ህዝባዊ እምቢተኝነት ለመፋን ሙከራ እያደረገ ነው።

የፖለቲካ ተንታኞች አፈናው ብሶትን እየወለደ ተቃውሞውን ያጠናክረዋል እንጅ አያበርደውም በማለት አገዛዙ ራሱን መልሶ እንዲያይ ምክራቸውን እየለገሱ ነው። የአሜሪካና የአውሮፓ መንግስታት የአፈና እርምጃው ችግሩን ይፈታዋል ብለው እንደማያምኑ ሰሞኑን ባወጡዋቸው መግለጫዎች ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ለ4ኛ ቀን በቀጠለው የባህርዳር የስራ ማቆም አድማ ተሳትፈዋል የተባሉ በርካታ ነጋዴዎች ታስረዋል። ነጋዴዎቹ ሱቆቻቸውን በግድ እንዲከፍቱ ተደጋጋሚ ጫና ሲደርስባቸው ቢቆይም በአቋማቸው በመጽናት አድማውን ቀጥለውበታል። በዚህ የተበሳጨው ገዢው ፓርቲ ዋና ዋና የሚላቸውን ነጋዴዎች እያፈላለገ በማሰር ላይ ነው።የአዴት ተራ፣ ህንጻ መሳሪያ እና መናኃሪያ አካባቢ ያሉ ኤሌክትሮኒክስ ድርጅት ባለቤቶች በብዛት መታሰራቸው ታውቋል።

የባህርዳር የስራ ማቆም አድማን ተከትሎ የፊታችን ሰኞ በታሪካዊቷ የጎንደር ከተማም የ3 ቀን የስራ ማቆም አድማ ለማድረግ ጥሪ ቀርቧል። አድማውን የሚያስተባብረው ቡድን፣ የአዲስ አበባ ህዝብ ለነጻነት በሚደረገው ትግል ተሳታፊ በመሆን አድማውን ተግባራዊ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርቧል።