አይ. ኤም.ኤፍ የኢትዮጵያን መንግስት የኢኮኖሚ ዕድገት ትንበያ እንደማይቀበል አስታወቀ

ሰኔ ፲፩ (አስራ አንድ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የኢትዮጵያ መንግስት በዘንድሮው ዓመት ከ 11 በመቶ በላይ የኢኮኖሚ ዕድገት እንዳስሚያስመዘግብ በተደጋጋሚ ሲገልጽ መቆየቱ ይታወሳል።

የዓለማቀፉ የገንዘብ ተቋም የአፍሪካ ዲፓርትመንት ምክትል ዳይሬክተር በሆኑት በሚስተር ማይክል አቲንጅ የተመራውና ከግንቦት 26 እስከ ሰኔ 7 ቀን 2004 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ቆይታ ያደረገው የ አይ. ኤም ኤፍ  ልዑክ ግን ፣ ይህን የኢትዮጵያ መንግሥት  የኢኮኖሚ ዕድገት ትንበያ እንደማይቀበለው ነው በግልጽ ያስታወቀው።

ልዑኩ የኢትዮጵያ መንግስት እያስመዘገብኩት ነው ያለውን ዕድገት  ዝቅ ያደረገው ፤ከ 50 በመቶ በታች ነው።

መንግስት ዘንድሮ  ኢኮኖሚው ከ 11 በመቶ በላይ ማደጉን ቢናገርም፤ የ አይ አም ኤፍ ልዑካን ግን የዘንድሮው ዕደገት 5 በመቶ ብቻ መሆኑን ነው  በግልጽ የተናገሩት።

አገሪቱ  ኤክስፖርት የምታደርጋቸውን ምርቶች በተለይም የጨርቃ ጨርቅና የቆዳ ምርቶች፣ እንዲሁም የማዕድን ውጤቶች መጠነኛ መሻሻል የሚያሳዩ ከሆነ፤ በቀጣዩ ዓመት 7 በመቶ ዕድገት ልታስመዘግብ እንደምትችል ተንብዮአል።

ሪፖርተር አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የኢትዮጵያ የገንዘብና የኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር  ባለሙያን ጠቅሶ እንደዘገበው፤የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት የዘንድሮው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ11.2 በመቶ እንዳደገና በሚቀጥለው ዓመትም ተመሳሳይ ዕድገት እንደሚጠብቁ ያቀረቡት መረጃ፣ በአይኤምኤፍ በኩል ተቀባይነት  ሳያገኝ ቀርቷል።

የአይኤምኤፍ ልዑካን  በጉብኝታቸው፤ ” የ ኢት ዮጵያ ኢኮኖሚ በተከታታይ ከ11 በመቶ በላይ አደገ”  የሚባለው  እንዴት እንደሆነ  ይገለጽላቸው ዘንድ ማብራሪያ መጠየቃቸውን ባለሙያው  ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ለጥያቄው በሰጡት ምላሽ ፤ ከተመዘገበው 11.2 በመቶ ዕድገት ከፊሉ በኢንቨስትመንት መገኘቱን፣ 5.6 በመቶ የሚሆነው ዕድገት  የመጣው ደግሞ የኢኮኖሚ ምርታማነት  በመጨመሩ ምክንያት  መሆኑን  ተናግረዋል።

እንደ ባለሙያው ገለፃ፤ የመንግስት ባለሥልጣናት ይህን ምክንያት በተደጋጋሚ በመግለጽ  ለማሳመን ጥረት ቢያደርጉም፣ የአይኤምኤፍ ልዑካን ግን የአገሪቱ ምርታማነት ከአምስት እስከ ስድስት በመቶ በየዓመቱ ከጨመረ፣ ከቁጥጥር ውጪ የሆነ የዋጋ ግሽበትና የአቅርቦት እጥረት ሊያጋጥም እንደማይችል በማስረዳት ምክንያቱን ውድቅ አድርገውታል።

እንዲሁም አገሪቱ ዝቅተኛ ምርታማነት ያለው የሰው ጉልበትና ዝቅተኛ የካፒታል መሠረት ያላት ከመሆኑ አኳያ ፤አጠቃላይ ዕድገቱን በተለይም “የአገሪቱ ግብርና በየዓመቱ በዘጠኝ በመቶ አድጓል” መባሉ እንዳልተዋጠላቸው  በግልጽ አሳውቀዋል- የ አይ.ኤም.ኤፍ ልዑካን።

በጉዳዩ ዙሪያ ጋዜጣው ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር የዘንድሮ የዋጋ ጭማሪ ፍጥነት ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የበለጠ ሆኖ ሳለ፣ የዋጋ ግሽበት እየቀነሰ ነው የሚባለው መግለጫ ተቀባይነት የሌለውና ማንንም የማያሳምን ነው ብለዋል፡፡

በቀላሉ በጤፍ፣ በወተት፣ በሥጋ፣ በአትክልትና ፍራፍሬና በቤት ኪራይ ላይ የተደረጉትን የዋጋ ጭማሪዎች ካለፈው ዓመት ጋር በማነፃፀር እውነታውን ማወቅ ይቻላል  ሲሉም አክለዋል።

በሌላ በኩል እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ለሦስት ወራት የገቢ ዕቃዎች መሸፈኛ የሚሆን የውጭ ምንዛሪ ክምችት የነበረ ቢሆንም፤ በአሁኑ ጊዜ ያለው የውጭ ምንዛሪ ክምችት  ወደ አንድ ወር ከሰባት ቀን መውረዱ ተዘግቧል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide