(ኢሳት ዜና–ሕዳር 8/2010) ጎንደር አጠገብ አዘዞ በሚገኘው የ24ኛው ክፍለጦር ወታደራዊ ካምፕ ላይ ጥቃት መፈጸሙን አርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ አስታወቀ።
ዛሬ ንጋት ላይ በተፈጸመው በዚሁ ጥቃት የካምፑ የተወሰኑ ቤቶች በቃጠሎ መውደማቸውን ንቅናቄው አስታውቋል።
በተያያዘ ዜና ከሱዳን ነዳጅ ጭኖ ሲጓዝ በነበረ ከባድ ተሽከርካሪ /ቦቴ/ ላይ በተወሰደ ርምጃ ተሽከርካሪው ከጫነው ነዳጅ ጋር መውደሙን አርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ ገልጿል።
የአማራ ክልል ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ተሽከርካሪው የተቃጠለው የመገልበጥ አደጋ ደርሶበት ነው ሲሉ በግል የፌስ ቡክ ገጻቸው አስታውቀዋል።
ከጎንደር በ7ኪሎ ሜትር ትርቃለች። በአቅራቢያዋ በሚገኘው የ24ኛው ክፍለጦር ካምፕ በይበልጥ ስሟ ይነሳል። አዘዞ።
ዛሬ ንጋት ላይ በዚሁ 24ኛ ክ/ጦር ካምፕ ላይ ጥቃት መፈጸሙን የሚያሳዩ መረጃዎች ለኢሳት ደርሰዋል።
በካምፑ የሚገኙ ቤቶች በእሳት መያያዛቸውን የሚገልጹት መረጃዎች አካባቢው በመንግስት ጦር በመከበቡ መጠጋት እንዳልተቻለም የሚያሳዩ ናቸው።
አርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ እንዳስታወቀው የንቅናቄው ታጣቂዎች በወሰዱት ርምጃ የካምፑ መጋዘን በከፊል ወድሟል።
የአካባቢው ነዋሪዎች መጋዘኑ በሚቃጠልበት ጊዜ ከፍተኛ የተኩስ ድምጽና ፍንዳታ ይሰማ እንደነበር ለኢሳት ገልጸዋል።
የጎንደር አየር መንገድና የጎንደር እሳት አደጋ ቡድን ቃጠሎውን መቆጣጠር ባይችሉ ኖሮ ካምፑ በከፍተኛ ደረጃ ጉዳት ይደርስበት እንደነበረ ለማወቅ ተችሏል።
በአሁኑ ሰዓት ካምፑና በዙሪያው ያሉ መንደሮች በልዩ ሃይልና በፌደራል ፖሊስ እንዲሁም በመከላከያ ሰራዊት እየተጠበቁ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።
በአዘዞ የ24ኛ ክ/ጦር ካምፕ ላይ የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ ተረኛ መኮንን የነበሩትና የዘብ ጠባቂዎች የታሰሩ ሲሆን በካምፑ ጭልጋ በር በሚባለው መጠበቂያ ማማ ላይ የነበሩ ሁለት ወታደሮች ከነትጥቃቸው መሰወራቸውን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በሌላ በኩል ትላንት አመሻሽ ላይ ከሱዳን ነዳጅ ጭኖ ወደ ሰሜን ጎንደር ሲጓዝ በነበረ ነዳጅ አመላላሽ ተሽከርካሪ ቦቴ ላይ ጥቃት መፈጹሙን አርበኞች ግንቦት ሰባት አስታወቋል።
በወታደር መኪና ታጅቦ የነበረው ተሽከርካሪ ጭልጋ ወረዳ ጓንግ ወንዝ ድልድይ ከመድረሱ በፊት ጥቃት የተፈጸመበት መሆኑን የገለጸው አርበኞች ግንቦት ሰባት በጥቃቱም ተሽከርካሪው ከጫነው ነዳጅ ጋር ሙሉ በሙሉ ሲቃጠል አሽከርካሪው ከባድ ጉዳት ደርሶበት ወደአይከል የህክምና ማዕከል መወሰዱን አስታውቋል።
ይህን ጥቃት በተመለከተ በግል የፌስ ቡክ ገጻቸው ላይ ‘’አደጋው የመገልበጥ ነው’’ ሲሉ የአማራ ክልል ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ገልጸዋል።
አቶ ንጉሱ እንደሚሉት የሰሌዳ ቁጥሩ ኢት 3 090485 የሆነ ነዳጅ የጫነ ተሽከርካሪ በደረሰበት የመገልበጥ አደጋ በእሳት ተያይዞ የተቃጠለ ሲሆን የጸጥታ አባላት በአካባቢው ክትትል እያደረጉ ነው። አርበኞች ግንቦት ሰባት እንዳስታወቀው በተሽከርካሪው ላይ ጥቃቱ ከተፈጸመ በኋላ የአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ማዋከብ እየተካሄደ ነው።