ሮበርት ሙጋቤ ለመጀመሪያ ጊዜ በሕዝባዊ መድረክ ላይ ታዩ

(ኢሳት ዜና–ሕዳር 8/2010)ሮበርት ሙጋቤ ከሁለት ቀናት የቁም እስር ቆይታ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በሕዝባዊ መድረክ ላይ መታየታቸው ታወቀ።

ስልጣኑን ለጊዜው የተቆጣጠረው ወታደራዊ ሃይል ሙጋቤ ስልጣናቸውን በፈቃዳቸው በሰላማዊ መንገድ እንዲለቁ ያስቀመጠው ቀነ ገደብ ዛሬ መጠናቀቁም ታውቋል።

ስልጣን እንዲለቁ የሚጠይቅ ሕዝባዊ ሰልፍ ለነገ ተዘጋጅቷል።

የስልጣን ዘመናቸው ሊያበቃ አንድ አመት የቀራቸው ዶክተር ሮበርት ገብርኤል ሙጋቤ የመሪነቱን ስፍራ ለባለቤታቸው ለማመቻቸት ምክትላቸውን ከወር በፊት ከስልጣን ማባረራቸው ለዛሬው ቀውስ ምክንያት መሆኑ ይገለጻል።

ከዚምባቡዌው የጦር ጄኔራል በስተጀርባ ሆነው ሙጋቤን ከስልጣናቸው ለማንሳት ነገር የሚጎነጉኑትም እኚሁ ተባራሪ ምክትል ፕሬዝዳንት ኢመርሰን ናንጋግዋል መሆናቸውን ዘገባዎች አመልክተዋል።

ሱቆች እንዲሁም ልዩ ልዩ ተቋማት ተከፍተው በተለመደው ተግባር ላይ መሆናቸው ቢገለጽም በከተማዋ ሃራሬ ያለው ጸጥታ ለአራተኛ ቀን ቀጥሏል።

ከቁም እስር ወጥተው ዛሬ በዚምባቡዌ ኦፕን ዩኒቨርስቲ ምረቃ ስነ ስርአት ላይ የተገኙትና ያገቷቸውን ጄኔራል ባለቤት ጭምር የመረቁት ሮበርት ሙጋቤ እሳቸውን በጊዜያዊ የሽግግር መሪ ለመቀየር የቀረበላቸውን አማራጭ እንደማይቀበሉ ገልጸዋል።

ጊዜዬን ሳልጨርስ መልቀቅ ሕገመንግስቱን የሚጥስና ቀውስ የሚጋብዝ ነው ሲሉም ተከላክለዋል።

ሆኖም የቀረበውን አማራጭ እንዲቀበሉና የክብር ስንብት እንዲያደርጉ የተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ ዛሬ ያበቃል።

በመጨረሻ ሰአት ሃሳቡን ይቀበሉ፣አይቀበሉ የተረጋገጠ ነገር የለም።

ሮበርት ሙጋቤ የክብር ስንብቱን ካልፈቀዱ በውርደት እንደሚባረሩም ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል።

በዚህም ለነገ ቅዳሜ ከፍተኛ የተቃውሞ ሰልፍ መዘጋጀቱ ታውቋል።

ሮበርት ሙጋቤ ዚምባቡዌን ከነጮች አገዛዝ ነጻ ለማውጣት በተደረገው ትግል ጉልህ ሚና የነበራቸውና የዚምባቡዌያን መመኪያ እንደነበሩ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ለ37 አመታት ስልጣንን የሙጥኝ በማለታቸው ግን ተሰሚነታቸው እየቀነሰ መምጣቱ ሲገለጽ ቆይቷል።

የቀድሞዋን ሮዲቪያን የአሁኗን ነጻይቷን ሀገር ዚምባቡዌን በ56 አመታቸው መምራት የጀመሩትና 37 አመታት በስልጣን ላይ የቆዩት የ93 አመቱ ሮበርት ሙጋቤ በአለም ላይ ከሚገኙ የሀገር መሪዎች በእድሜ ትልቁ ናቸው።

የእንግሊዟ ንግስት ዳግማዊት ኤልሳቤጥ በ91 አመት ከ206 ቀን ይከተሏቸዋል።

ሙጋቤ ከሶስት ወር በኋላ እንደአውሮፓውያኑ አቆጣጠር የካቲት 21/2018 94 አመት ይሞላቸዋል።

ከካሜሮኑ ፖል ቢያና ከኢኳቶሪያል ጊኒው ቴዋዶሮ ኦቢያንግ ኒዬማ ቀጥሎ በአለም ረዥም ዘመን በስልጣን ላይ የሚገኙ ሶስተኛ መሪም ሆነው ተመዝግበዋል።