የካቲት ፩ ( አንድ )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በየካቲት ወር 2008 ዓ.ም በአዲስአበባ ከተማ ተግባራዊ ሊሆን ሲል በታክሲ አሽከርካሪዎች የሥራ ማቆም አድማ መንግሥት ተገዶ አፈጻጸሙ እንዲራዘም የወሰነው የትራፊክ ደህንነት ደንብ ቁጥር 208/2003 ጥቂት ማሻሻያዎችን በማድረግ ሰሞኑን ጸድቆ በሥራ ላይ ውሎአል፡፡
ደንቡ በተደጋጋሚ ጥፋት የሚገኝባቸው አሽከርካሪዎችን መንጃ ፈቃድ እስከመንጠቅ የሚደርስ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ሲሆን ፣ ባለፈው ዓመት ተግባራዊ ሊሆን ሲል የታክሲ አሽከርካሪዎች፣ ረዳቶችና ባለንብረቶች የሥራ ማቆም አድማ በማድረግ በመቃወማቸው ምክንያት በአገዛዙ ውሳኔ የደንቡ አፈጻጸም መካከል የቅጣት ክፍያው ብቻ እንዲፈጸም፣ የሪከርድና የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ የማገድ ሥራ አፈጻጸም ለሶስት ወራት እንዲራዘም ተወስኖ ነበር። ደንቡ በአሁኑ ሰዓት አንዳንድ ማሻሻያዎች ተደርገውለት በሥራ ላይ እንዲውል ተወስኗል፡፡ በደንቡ ውስጥ ተቃውሞ አስንስተው የነበሩ ድንጋጌዎች መካከል ተደጋጋሚ የትራፊክ ደንብ ጥሰት ጥፋት ፈጽመው የሚገኙ አሽከርካሪዎች ሪከርድ እስከ ስድስት ጊዜ እየተመዘገበ በገንዘብ ሲቀጣ ከቆየ በኃላ የመንጃ ፈቃዱ እንደሚሰረዝ ቀድሞ ተቀምጦ የነበረው ድንጋጌ በተሻሻለውና ሰሞኑን በጸደቀው ደንብ ውስጥ እንዲቀጥል ተደርጓል፡፡
በአዲስ ማሻሻያነት እንዲገቡ ከተደረጉት ድንጋጌዎች መካከል አልኮል ጠጥቶ በማሽከርከር፣ መብራት ጥሶ በማሽከርከር የትራፊክ አደጋ ጉዳት ያደረሰ አሽከርካሪ ከሕግ ተጠያቂነት በተጨማሪ መንጃ ፈቃዱ እስከ አንድ ዓመት እንዲታገድ የሚደነግገው አንቀጽ ይገኝበታል፡፡
በደንቡ ላይ በተለይ የታክሲ አሽከርካሪዎች አምና የሥራ ማቆም አድማ በመምታት ካቀረቡዋቸው ጥያቄዎች መካከል ደንቡ በቂ የተሸከርካሪና የእግረኛ መንገዶች፣ በቂ የትራፊክ ምልክቶች፣ በቂ የመኪና ማቆሚያ (ፓርኪንግ) በሌሉበት ሁኔታ እንዲሁም በሙስናና ብልሹ አሠራር የሚታወቁ የትራፊክ ፖሊሶች በበዙበት ሁኔታ ተግባራዊ መሆኑ አሽከርካሪዎችንና የታክሲ ባለንብረቶችን ሆን ብሎ ለጉዳት ከመዳረግ በስተቀር የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ ሚና አይኖረውም ፣ በቅድሚያ ችግሮቹ ይፈቱ የሚሉት ይገኝበታል፡፡
አወዛጋቢውን ደንብ በቀጥታ ከሚያስፈጽሙ መ/ቤቶች መካከል በአዲስአበባ ከተማ አስተዳደር የመንገድ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲን በዋና ዳይሬክተርነት የሚመሩት አቶ ገነቱ ደሳለኝ፤ የጠ/ሚኒስትር አቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝ ታናሽ ወንድም ናቸው።
አንድ ስለደንቡ አስተያየቱን የጠየቅነው የታክሲ ሹፌር እንደተናገረው ቀደም ሲል አድማ በማድረግ አቅርበውት የነበረው ጥያቄ በትክክል ይመለስ፣ አይመለስ መረጃ እንደሌለው፣ ያልተመለሰ ከሆነ ግን በዚህ ዓይነት ሕግ ስር ሆኖ የታክሲ ሥራ መስራት አዋጪ ስላልሆነ በቀጣይ በምንወስደው እርምጃ ዙሪያ በተለይ የታክሲ ሹፌሮች ሊመክሩ እንደሚገባ አሳስቦአል ፡፡