የኦሮምያ ከተማ ልማት ቢሮ ሰራተኞች በጥልቅ ተሃድሶ ስም የቀረበውን ሪፖርት ተቃወሙ

የካቲት ፩ ( አንድ )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከሁለት ሳምንት በፊት በአዳማ ከተማ ቶኩማ ሆቴል የተሰበሰቡት የኦሮምያ ከተማ ልማት ቢሮ ሰራተኞች፣ በአዲሱ ሃላፊያቸው የቀረበውን ሪፖርት አጣጥለውታል። ሃላፊው ፣” መንግስት ደሞዝ በመጨመር፣ ቤት ሰርቶ በመስጠትና የኑሮ ሁኔታችሁ እንዲሻሻል ቢያደርግም ፣ እናንተ ግን በተቀራኒው የምትሰሩት ስራ መንግስትን የሚያስወቅስ በመሆኑ ይህ እንዳይቀጥል ቃል መግባት አለባችሁ” ብለው ሲናገሩ፣ ሰራተኞቹ በበኩላቸው “ እርስዎ ገና አዲስ ተሹመው የመጡ ነዎት፣ ስለእኛ የኑሮ መሻሻል መረጃውን እንዴት አገኙት፣ በእኛ በኩል መረጃውን ለእርስዎ ጽፎ የሰጠዎት አካል ይኖራልና ያ አካል መጥቶ ካላነጋገረን ስብሰባውን አንቀጥልም” በማለታቸው ስብሰባው ለሰአታት ተቋርጧል።
የቢሮ ሃላፊው የሰራተኞችን ጠንካራ አቋም በማየት፣ ጽሁፉ በሲቪል ሰርቪስና መልካም አስተዳደር ቢሮ በአቶ ሺመልስ በኩል ተዘጋጅቶ እንደተሰጣቸው በማመናቸው ሰራተኞች አቶ ሺመልስ ቀርበው ማብራሪያ ካልሰጡ ስብሰባውን አንቀጥልም በማለት በድጋሜ አቋማቸውን አሳውቀዋል። በማግስቱ አቶ ሺመልስ ተገኝተው ሰራተኞች እስካሁን ለተፈጠረው ችግር ሃላፊነት እንዲወስዱ በማስፈራራት ለማሳመን ጥረት ቢያደርጉም አልተሳካለችውም።
ሰራተኞች “ እኛ እንዴት ባለ ሥቃይ ውስጥ እንዳለን ከእኛ በላይ ማንም ሊያውቅ አይችልም፡፡ በእርግጥ እናንተ ስትሾሙ እንዳላችሁት ህይወታችሁና ኑሮኣችሁ ተሻሽሎ ሊሆን ይችላል፣ ቤት ተሰጥቷችሁ ከቤት ችግር ተላቃችሁም ሊሆን ይችላል፣ መኪና ስለተመደበላችሁ የትራንስፖርት ችግሩን ልትረሱት ትችላላችሁ ወይም ቀድሞ በነበራችሁበትም ችግሩ አልደረሰባችሁ ሊሆን ይችላል፡፡ እኛ በእናንተ ባልተዘጋጀው ፣ግን እንዲነበብ በተደረገው ጽሁፍ የተገለጸውን ህይወት የምናውቀው ከእናንተ አፍ ሲወጣ ብቻ ነው፤ በቁስላችን እንጨት እንድትሰዱ አንፈቅድም ፡፡ የራሳችሁን ችግር የሲቪል ሰርቪሱ ነው ብላችሁ በተለመደው መንገድ ጥፋቱን ወደ እኛ/ሰራተኞች ለማላከክ የምታደርጉትን ከእንግዲህ አንቀበልም ፡፡ ያለፈውን ዓይነት ማስፈራሪያም ሆነ የሌለውን አለ፣ የራሳችሁን የኑሮ መሻሻል የእኛ አድርጋችሁ የምታቀርቡትን አንቀበልም፣ ለውጥ እንፈልጋለን፡፡ ሥቃያችን ከአቅማችን በላይ ሆኗል፤ ሸክማችን ከብዷልና ከዚህ የባሰና የከፋ አንዳች የሚመጣብን የለም፣ ይልቁንስ በሥቃያችን እንድትሳለቁ ያለመፍቀዳችን ልታውቁት ይገባል፡፡ ›› በማለት ብሶታቸውን ገልጸዋል።
ሰራተኞች የኦፒዲዮ ተወካዮች ራሳቸውን ከህወሃት ተጽእኖ ነጻ እንዲያወጡ እና የህዝባቸው ተወካይ እንዲሆኑ አበክረው በመናገራቸው ሰብሳቢው “ ከዚህ ውጭ ለእናንተ የምሰጠው መልስ የለኝም ብለው ስብሰባውን አቋርጠው ወጥተዋል።
አዲሱ አመራር የሰራተኛውን ችግር መረዳቱንና አስፈላጊውን ማሻሻያ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ቢገልጽም፣ ከሰራተኛው የሚጠበቀውን “ይጥፋተኝነት” ቃል ሳያገኝ ስብሰባው ያለ ውጤት መበተኑን ምንጮች ለኢሳት ገልጸዋል።