አንድነት ፓርቲ ጀሃዳዊ ሀረካትን አጣጣለው

ጥር ፳፱ (ሀያ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ፓርቲው ” በ‹‹ጀሃዳዊ ሃረካት›› ትረካ የሙስሊሙን ማህበረሰብ ጥያቄ ማዳፈን አይቻልም!” በሚል ርእስ ባወጣው መግለጫ፣ በገዢው ፓርቲ ድርጊት ማፈሩንና ማዘኑን ገልጿል። ገዥው ፓርቲ  ዜጎች በማንኛውም መንገድ የሚያነሱትን ጥያቄ በግልጽና በውይይት መፍታት ያለመፈለጉ ግልጽ ሀገራዊ አደጋ እየሆነ መምጣቱ እየታየው ነው የሚለው አንድነት፣ “ኢትዮጵያን የምታክል ትልቅ ሀገር እያስተዳደረ ባለ መንግሥት” ማዘኑንም አልሸሸገም።

አንድነት በኢትዮጵያ ሕዝብ ግብር የሚተዳደረው ነገር ግን የገዥው ፓርቲ መሳሪያ በመሆን የሕዝብ  ጥያቄዎችን ለማፈን ተባባሪ መሳሪያ ሆኖ እያለገለ ያለው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ‹‹ጀሃዳዊ ሃረካት›› በሚል የተሰናዳና እንደተለመደው የሙስሊሙን ህዝብ ጥያቄን ለማዳፈን የተዘጋጀ አይነት ትረካ ሲያቀርብ የመጀመሪያው አለመሆኑን አስታውሷል።

ዶክመንታሪዎች የሚሰጣቸው ርዕስ ግዝፈትና የአጽመ ታሪካቸው ትረካ ልልነት ከተራ ድራማም ያነሰ ነው ሲል ፣ በኢቲቪ ትናንት የተላለፈውን ፊልም ያጣጣለው አንድነት፣ ትረካው የቀረበው  የሙስሊሙን አንድ ዓመት የዘለቀ ግልፅ ጥያቄ ፊት ለፊት ተወያይቶ በመመለስ ፋንታ በእጅ አዙር ለማድበስበስ ፣ በዜጎች ላይ የስነ-ልቡና ጫና በመፍጠር በፍርሓት ውስጥ አድርጎ ለመግዛት በማለም ፣  መንግሥት እጁን አስረዝሞ በኃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ በመግባት የሚያደርገውን የአድራጊ ፈጣሪነት ስራ ‹‹ሕግ ማስከበር›› የሚል ሽፋን በመስጠት የማደናገር ስራ ለመስራት  ነው ብሎአል፡፡

ይህ ዶክመንተሪ በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት አራተኛ ወንጀል ችሎት የዕግድ ትእዛዝ ቢተላለፍበትም በማናለብኝነትና ሥልጣንን ካለአግባብ በመጠቀም ያለምንም ይግባኝ በከፍተኛው ፍ/ቤት ፕሬዚዳንት ተሽሮ ለኢትዮጵያ ህዝብ እንዲተላለፍ መደረጉን ስንመለከት፣ ራሱ ህግ የሚጥስ ገዢ ፓርቲ እንዴት የሌሎችን ህግ ሊያስከብር ይችላል በማለት ጠይቋል።

ፓርቲው በመጨረሻም ”  ‹‹ጀሃዳዊ ሃረካት›› የሚል ትረካ በማቅረብ የሙስሊሙን ጥያቄ ማዳፈን አይቻልም፡፡ ዶክመንተሪው የሙስሊሙ ማህበረሰብ ጥያቄ መልስ ሊሆንም አይችልም፡፡” ብሎአል።በተመሳሳይ ዜና ኢቲቪ ያስተላለፈው ፊልም የመንግስትን ማንነት ከማጋለጥ ባለፈ ያስገኘው ለውጥ እንደሌለ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን በማነጋገር ዘጋቢያችን የላከው ሪፖርት ያሳያል። በተለያዩ መዝናኛ ቤቶች የሚገኙ ወጣቶች ጉዳዩን ሲወያዩበት መዋላቸውን የገለጠው ዘጋቢያችን፣ ድራማው ከአቀነባበር ጀምሮ የታየበት ችግር ህዝቡ የመንግስትን ትክክለኛ ማንነት እንዲረዳ እንዳደረገው ገልጿል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የድምጻችን ይሰማ መሪዎች ሰብሳቢ የሆኑት አቶ አቡበክር አህመድ ሲመረመሩ የሚያሳይ ቪዲዮ በዩቱዩብ ከተለቀቀ በሁዋላ፣ በርካታ ኢትዮጵያውያን በማህበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች ላይ በመንግስት ማፈራቸውን እየገለጡ ነው።