ነሀሴ ፳፱ (ሀያ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የአቶ መለስ ዜናዊን እረፍት ተከትሎ በሀገሪቱ ሊስተካከሉ የሚገባቸው የሰብዓዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ መብቶች ከበፊቱ በባሰ ሁኔታ መታፈናቸውን ቀጥለዋል ሲል አንድነት ለፍትሕ እና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ገለጸ።
አንድነት ፓርቲ ፦”የፍኖተ-ነፃነት ጋዜጣ መታገድ፤አምባገነናዊው ስርዓት አፈናውን አጠናክሮና አባብሶ መቀጠሉን የሚያሳይ ድርጊት ነው” በሚል ርዕስ ባወጣው መግለጫ፤የ አቶ መለስን ሞት ተከትሎ በሀገሪቱ ሊስተካከሉ የሚገባቸው የሰብዓዊ፣የዲሞክራሲያዊና ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብቶች ከበፊቱ በባሰ ሁኔታ እየተጨፈለቁ መምጣታቸው እንደሚያሳስበው ገልጿል።
“ እየታዬ ያለው ድርጊት ሀገሪቱን ወደ ባሰ ሁኔታ የሚከታት በመሆኑም በአስቸኳይ እንዲቆም እና የኢትዮጵያ ህዝብም እንዲታገለው አጥብቀን እንጠይቃለን። “ብሏል- አንድነት።
“ሀዘን ላይ ቆይተናል” ሲሉ የነበሩት የስርዓቱ መሪዎች ጋዜጣን መዝጋትና ዲሞክራሲያዊ መብትን መገደብ ፤ የቀጣዩ የአፈና ስርዓታቸው ማሟሻ አደርገውታል” ያለው አንድነት፤ በፍኖተ ነፃነት ላይ የተወሰደው ህገወጥ እርምጃ እንዲታረም ለሚመለከተው አካል የቀረበው ጥያቄ ምላሽ ሊያገኝ አለመቻሉን አመልክቷል።
አቶ መለስ ከቦታቸው መገለላቸውን ተከትሎ ፍትሕ ጋዜጣ መታገዱ እና ዋና አዘጋጁ ተመስገን ደሳለኝም የዋስ መብት ተነፍጎ ለእስር መዳረጉ ይታወሳል።
ሆኖም ከጥቂት ቀናት በሁዋላ ክሱ እንዲቋረጥ ተደርጎ ተመስገን ከእስር ተለቋል።
ጋዜጠኛ ተመስገን መፈታቱን ተከትሎ ፍትሕ ጋዜጣ ዳግም የህትመት ብርሀን ታይ ይሆናል ብለው ብዙዎች ተስፋ ባደረጉበት ሁኔታ፤ ይባስ ብሎ የአንድነት ፓርቲ ልሳን የሆነችው ፍኖተ ነፃነት መታገዷ፤አዲሱ አመራር ፕሬሱን በተመለከተ ሊከተለው ያሰበውን አስፈሪ የአፈና መንገድ አመላካች ነው ሲሉ የተቃዋሚ ፓርቲዎችና ጋዜጠኞች ከወዲሁ ክስ እያሰሙ ነው።
ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት የህግ አግባብ በሌለው ውሳኔ ፍኖተ-ነፃነትን አላትምም ማለቱ ህገ ወጥ በመሆኑ፤ በአስቸኩዋይ ይታረም ዘንድ የማተሚያ ቤቱን ም/ዋና ሥራ አሥፈፃሚ አቶ ሽታሁን ዋለን ማነጋገሩን የጠቀሰው የአንድነት የህዝብ ግንኙነት ክፍል፤ የማተሚያ ቤቱ ሀላፊዎች ግን በትዕቢትና በምን ታመጣላችሁ መንፈስ ‹‹ጋዜጣዋን አናትምም!ሂዱ የምትፈልጉትን አድርጉ!››የሚል ምላሽ መስጠታቸውን ጠቅሷል።
እንደ ፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ገለፃ፤የማተሚያ ቤቱ ሌላ ሃላፊ ፍኖተ-ነፃነት ጋዜጣ የታገደችው፤ የአቶ መለስን ሞት ተከትሎ በወጣው እትም ደስ ያልተሰኘው የማተሚያ ቤቱ ማኔጅመንት ባሳለፈው ውሳኔ ነው ሲሉ፤ ምክትል ስራ አስፈፃሚው ደግሞ ‹‹ማተም የማንችለው የመፅሀፍ ጨረታ ስላሸነፍን ነው›› የሚል የተለየ መልስ ሰጥተዋል፡፡
“ፓርቲያችን ከተጨባጭ ምንጮች ባገኘው መረጃ መሰረት ጋዜጣችን የተዘጋችው የማተሚያ ቤቱ ሃላፊዎች በሰጡት መሰረት የሌላቸው ምክንያቶች ሳይሆን፤ የስርዓቱ ቁንጮዎች በሆኑት ግለሰቦች ቀጭን ትእዛዝ ነው፡፡”ያለው አንድነት ፓርቲ፤ የማተሚያ ቤቱ ሃላፊዎች ድርሻ፦ የተሰጣቸውን ትዕዛዝ ማስፈፀም ብቻ ነው ብሏል።
ፍኖተ ነፃነት የፖለቲካ ፓርቲ ልሳን እንደመሆንዋና ፓርቲው ደግሞ ያለበትን ሃገራዊ ሃላፊነት መወጣት እስካለበት ድረስ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሞት ተከትሎ የሃገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች ምን መልክ እንደሚኖራቸው አመላካች የሆኑ፤ ትንታኔዎችን በልዩ ዕትም ዓርብ ነሐሴ 18 ቀን 2004 ዓ.ም ለንባብ ማብቃቷን የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ክፍል አውስቷል።
“ይህም ፓርቲው ለተሸከመው ሃገራዊ ራዕይ እንዴት ቁርጠኛ እንደሆነ የሚያሣይና ሃላፊነቱን እንዴት በብቃት እንደተወጣ የሚያመላክት እንደሆነ እናምናለን፡፡”ያለው አንድነት፤ “ያደረግነው፤ ከአንድ የፖለቲካ ፓርቲ የሚጠበቅን ተግባር ነው፡፡ ይህ አበረታች ስራ እንጅ፤ የሚኮነን ሊሆን አይችልም”ብሏል።
“ይሄ የአንድነት ጥንካሬ ያልተዋጠላቸው ተተኪ አምባገነኖች በሀገሪቱ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ ተከትሎ ጠንካራ ሃሳብ ያላቸውን ኢትዮጵያውያን በማስተናገድ እንደገና ዓርብ ነሐሴ 25 ቀን 2004 ዓ.ም የጋዜጣው ዝግጅት ክፍል በመረባረብ ያዘጋጀውን ልዩ ዕትም ፦ “ እንደውም ከዚህ በሁዋላ አናትምም!” በማለት ጋዜጣችንን አፍነዋል፡፡”ሲል ፓርቲው በመግለጫው አመልክቷል።
“ አፈናቸውንም በቃል እንጅ በወረቀት አልሰጡንም፡፡”ያለው አንድነት ፓርቲ፤”ይህም ከፊት ለፊታችን አስፈሪ አምባገነን ተተኪዎች እየመጡም እንደሆነ ይጠቁመናል፡፡”ብሏል።
በመጨረሻም፦”አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ፤ ልሳኑ በስርዓቱ አምባገነኖች ሲዘጋበት ዝም ብሎ እንደማያይ ለማረጋገጥ እንወዳለን፡፡”ያለው አንድነት ፓርቲ፤ “ይህ አይን ያወጣና ያፈጠጠ ተግባር ከኢትዮጵያችን እስከሚወገድና ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሳይሸራረፉ እስከሚረጋገጡ ድረስ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በመሆን እስከ መጨረሻው እንታገለዋለን፡፡”ብሏል።