አንድነት ፓርቲ በጎንደር ቅስቀሳ እያደረገ ነው

ሰኔ ፳፪ (ሃያ ሁለት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና :-ፓርቲው ሰኔ 30 ቀን በጎንደር ከተማ አደባባይ ለሚያካሂደው የተቃውሞ ሰልፍ በከተማዋና በዙሪያ ወረዳዎች የጥሪ ወረቀቶችን በመበተን ላይ እንደሚገኝ የሰሜን ኢትዮጵያ አደራጅ እና የብሄራዊ ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ አእምሮ አወቀ ለኢሳት ገልጸዋል።

በምእራብ አርማጭሆ በአብራሀ ጅራ ከተማ አለልኝ አባይ፣  እንግዳው ዋኘው፣ አብርሀም ልጃለም እና አንጋው ተገኘ የተባሉ የአንድነት ፓርቲ አባላት ወረቀቶችን ሲበትኑ ዛሬ ከቀኑ 7 ሰአት አካባቢ በደህንነቶች ታስረው መወሰዳቸውን አቶ አእምሮ ተናግረዋል

የሰላማዊ ሰልፉ ማሳወቂያ ደብዳቤ አልቀበልም ብሎ ለነበረው የጎንደር ከተማ ከንቲባ ጽህፈት ቤት  ደብዳቤውን በፖስታ መላካቸውንና መድረሱን ማረጋገጣቸውን ተወካዩ ገልጸዋል።

በመጪው ሰኔ 30 በሚካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ በርካታ ህዝብ ይገኛል ብለው እንደሚጠብቁ አቶ አእምሮ ተናግረዋል።

የጎንደር ከተማ የቀበሌ 6 እና 7 ነዋሪዎች በቅርቡ በራሳቸው ተነሳሽነት የተቃውሞ ሰልፍ ማድረጋቸው ይታወሳል።