አንድነት ፓርቲ በደሴ የተሰካ የተቃውሞ ሰልፍ አደረገ

መጋቢት ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የሚሊዮኖች ድምጽ በሚል የተጀመረው ሁለተኛ ዙር የአንድነት ፓርቲ እንቅስቃሴ እሁድ መጋቢት 28 ቀን 2006 ዓም በደሴ ከተማ የተካሄደ ሲሆን፣ በተቃውሞ ሰልፉ ላይ በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች በሰልፉ ላይ ተገኝተዋል።

የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ የሆኑት አቶ ሀብታሙ አያሌው የዝግጅቱ አላማ ህዝቡ ወደ አደባባይ ወጥቶ ችግሩን እንዲናገር፣ እንዲተነፍስ፣ የህዝቡን ችግሮች ለማወቅ እና ህዝቡ ከፍርሃት በወጣ ስሜት ይህንን አስከፊ ስርአት እንዲቃወም ለማድረግ በመሆኑ፣ በሰልፉ ላይ የታየው ውጤት አበረታች መሆኑን ገልጸዋል።

ይህ አስከፊ ስርአት የተመሰረበት ዋነኛ ጉልበት ምን እንደሆነ አንድነት ለመለየት ጥረት ማድረጉን የገለጹት አቶ ሃብታሙ ፣ የአገዛዙ ጉልበት የተመሰረተው በመሬት ላይ መሆኑን ማወቁንና ህዝቡም ይህን ማንጸባረቁን ገልጸዋል።

አቶ ሃብታሙ አንድነት ፓርቲ በመሬት ላይ ያለውን አቋም ወደ ገጠር በማውረድ የገጠሩን ህዝብ ለማንቀሳቀስ ማቀዱንና ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩንም ገልጸዋል።

አቶ ሃብታሙ “ህዝቡ የተበጣጠሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ተሰባስበው እንዲታገሉ መጠየቁንም” ገልጸዋል። አንድነት ፓርቲ በመጪው እሁድ በአዲስ አበባ የተቃውሞ ሰልፍ የጠራ ሲሆን፣ የሰልፉ ዋና አላማ በከተማዋ እየተበላሸ የመጣውን አስከፊ የኑሮ ውድነት እና የማህበራዊ አገልግሎትን መቃወም ነው።