ሐምሌ ፫( ሦስት )ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና :-በኢትዮጵያ ያለውን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት፣ የኑሮ ውድነት እና የፍትህ እጦት ለመቃወም ፓርቲው በጎንደርና በደሴ የጀመረውን ቅስቀሳ ወረቀቶችን በመበተን፣ እና በመኪና ላይ በመሆን በየሰፈሩ በመዘዋወር በድምጽ ማጉያ የትግል ጥሪ እያስተላለፈ ነው።
በደሴ ከተማ በማስተባበር ላይ የሚገኙት የአንድነት ፓርቲ ብሄራዊ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ዘካርያስ የማነብርሃንና የፍኖት ነጻነት ጋዜጠኛ የሆነዉ አቶ ወንደወሰን ክንፈ ታግተው መለቀቃቸውን ከፓርቲው ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
የደሴ ከንቲባ በመጪው እሁድ ምንም አይነት ሰላማዊ ሰልፍ እንዳይደረግ ቢከለክልም አቶ ዘካርያስ የማነብርሃን ግን ተቃውሞውን ከማድረግ የሚከለክላቸው ነገር እንደሌለ ገልጸዋል
በተመሳሳይ ዜናም በአዲስ አበባ ቄራ አካባቢ የፓርቲውን ወረቀቶች በትነዋል የተባሉ አቶ ዳንኤል ፈይሳ፣ አቶ ስንታየሁ ቸኮልና አቶ አበበ ቁምላቸው ተይዘው ከታሰሩ በሁዋላ ፍርድ ቤት ቀርበዋል። ፖሊስ “አንድነት የሚባል ፓርቲ መኖሩን እስከማረጋገጥ ድረስ የጊዜ ቀጠሮ ይሰጠኝ” በማለት ፍርድ ቤቱን የጠየቀ ሲሆን፣ ፍርድቤቱም የፖሊስን ጥያቄ ተቀብሎ የ10 ቀናትየጊዜ ቀጠሮ ፈቅዷል። እስረኞቹም ወደ ማረሚያ ቤት ተልከዋል።
በየካ ክ/ከተማ ደግሞ አቶ ብሩክ አሻግሬ እና አቶ ወንድይፍራው ተክሌ የተባሉ የፓርቲው አመራሮች ታስረው በዋስ መለቀቃቸው ታውቋል።