የኮንዶሚኒየም ተመዝጋቢዎች ገንዘባቸውን ከንግድ ባንክ ውጭ ባሉ የግል ባንኮችም ማስቀመጥ ይችላሉ ተባለ

ሐምሌ ፫( ሦስት )ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና :-መንግስት በ10/ 90 ወይም በ20 / 80 የቁጠባ ስርአት የኮንዶሚኒየም ቤት ለመስራት የሚፈልጉ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገንዘባቸውን የመንግስት ንብረት በሆነው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብቻ እንዲያስቀምጡ ትእዛዝ ማስተላለፉ የግል ባንኮችን የሚያዳክም ነው የሚል ትችት ሲቀርብ

ሰንብቷል።

ገንዘባቸውን በግል ባንኮች ያስቀምጡ የነበሩ ደንበኞች ደንበኝነታቸውን  እየሰረዙ በንግድ ባንክ ማስቀመጥ ከጀመሩ ባንኮች በደንበኛ እጥረት ከገበያ ውጭ ይሆናሉ በማለት አንዳንድ የባንክ ባለሙያዎች ቅሬታቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትር ሐይለማርያም እና ለብሄራዊ ባንክ ሀላፊዎች አቅርበዋል። በመንግስት በኩል የተሰጠው መልስ ” ንግድ ባንክ ለረጅም ጊዜ እና በዝቅተኛ ወለድ የሚያበድር በመሆኑ፣ አሰራሩ ለባንኩም የሚጠቅም አይደለም፣  ባንኩ የመንግስትን ጥያቄ

የተቀበለው በጫና ነው ፣ ይህን አገልግሎት እሰጣለሁ የሚል ባንክ ካለ መጠቀም ይችላል” የሚል ነው።

በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየታቸውን የጠየቅናቸው የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት  ወ/ሮ ሙሉ ሰለሞን የግል ባንኮች ” አሰራሩ ይጥቀመንም አይጠቀመንም እኛው ራሳችን መወሰን ነበረብን” የሚል መልስ መስጠታቸውን ተናግረዋል። የእኛ ጥያቄ የሚሰጠው እድል ለሁሉም እኩል ይሁን የሚል ነው ሲሉም ተናግረዋል::

“የኮንዶሚኒየም ምዝገባ በማለቁ ለሁለተኛው ዙር መንግስት እድሉን ለግል ባንኮች እንደሚሰጥ ተስፋ አደርጋለሁ” ያሉት ፕሬዚዳንቷ፣ ቀደም ብሎ በወጣው መመሪያ የግል ባንኮች ምን ያክል ጉዳት እንደደረሰባቸው ለማወቅ አለመቻሉንም አክለዋል፡፡

በመጀመሪያው ዙር የኮንዶሚኒየም መርሀግብ ከ850 ሺ እስከ 1 ሚሊየን የሚጠጉ ሰዎች ይመዘገባሉ የሚል እቅድ እንደነበር ይታወቃል።