ግንቦት ፲፪ (አስራ ሁለት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ ባወጣው መግለጫ በዝዋይ በፖለቲካ እስረኞችና ጋዜጠኞች ላይ ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደሚፈፀምባቸው ለመረዳት መቻሉን ገልጿል።
የእስረኞች ቤተሰቦች ለጥየቃ በሚሄዱበት ጊዜ መጎብኘት እንደማይችሉና ይዘውት የሄዱትን ምግብ ይዘውት ወደ አዲስ አበባ እንዲመለሱ ፓርቲው በመግለጫው ጠቅሷል።
“እስረኞቹ የሚፈፀምባቸውን በደል ለማሳወቅ ለ3 ቀናት የሚቆይ የርሃብ አድማ ማድረጋቸውን ተከትሎ የዝዋይ ማረሚያ ቤት ኃላፊ ከአራት ወራት በፊት ‘ማንኛውም ቤተሰብ እስረኞችን ለመጠየቅ ወደዚህ ቦታ ድርሽ እንዳይል’ የሚል ማስጠንቀቂያ በመስጠታቸው የእስረኞች ቤተሰቦች እስረኞቹ ስላሉበት ሁኔታ ማወቅ ባለመቻላቸው ጭንቀት ውስጥ መግባታቸውን ፓርቲው አክሎ ገልጿል።
ፓርቲው የእስረኞቹ ሕገ-መንግሥታዊ መብት ተጠብቆ ከቤተሰቦቻቸውና ከዘመዶቻቸው እንዲሁም ከጠበቆቻቸው ጋር የሚገናኙበት መንገድ በአስቸኳይ እንዲመቻች እንዲሁም በእስረኞች ላይ የተፈፀመው ሕገወጥ ድርጊት በገለልተኛ ወገን ተጣርቶ ለሕዝብ ይፋ እንዲሆን ጠይቋል።
ሀገር ዓቀፍና ዓለማቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ደርጅቶች፤ ዲፕሎማቶች፤ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት ሃላፊዎች፤ ጋዜጠኞችና ሌሎችም ወገኖች በእስረኞች ላይ እየተፈፀመ ያለውን ህገ-ወጥ ድርጊት ለማስቆምና የፖለቲካ እስረኞችን ለመታደግ እንዲሁም የህግና የሞራል ግዴታን ለመወጣት እንዲረባረቡ ፓርቲው ጥሪ አቅርቧል፡፡