በአዲስ አበባ ቤቶቻቸው የፈረሱባቸው ሰዎች ብሶታቸውን እየገለጹ ነው

ግንቦት ፲፪ (አስራ ሁለት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ካለፈው ሳምንት ጀምሮ እንደ አዲስ ተጠናክሮ በቀጠለው በህገወጥ መንገድ ተሰርተዋል የተባሉትን ቤት የማፍረስ ዘመቻ በርካታ ነዋሪዎችን ሜዳ ላይ እየበተነ መሆኑን ነዋሪዎች ይናገራሉ።

አለም ባንክ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ በርካታ ነዋሪዎች ባልተጠበቁት ሰአት ቤታቸው እንዲፈርስ በመደረጉ ነፍሰጡሮች ሳይቀር ለከፍተኛ ችግር ተደርገው ነበር። የመንግስትን ድርጊት የተቃወሙትም እንዲሁ እየተደበደቡ አንዳንዶች እንዲታሰሩ ተደርጓል።

ዛሬ ማክሰኞ ሰሚት እየተባለ በሚጠራው አካባቢ በርካታ ቤቶች በመፍረሳቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ ቤተሰቦች መጠለያ አልባ ሆነዋል። የመንግስትን ህገወጥ ድርጊት የተቃወሙት በፖሊሶች መደብደባቸውን ነዋሪዎች ገልጸዋል

የአዲስ አበባ መስተዳድር በገጠመው ከፍተኛ የቦታ እጥረት ህወገወጥ ቤቶች ብሎ የሰየማቸውን ሁሉ በማፍረስ በሺዎች የሚቆጠሩ የከተማዋን ነዋሪዎች ቤት አልባ አድርጓቸዋል።

የቀድሞው የኮሚኒኬሽን ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ኤርምያስ ለገሰ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ከ150 ሺ በላይ በአዲስ አበባ ዙሪያ ይኖሩ የነበሩ አርሶደአሮች መሬታቸውን ተነጥቀው የገቡበት እንደማይታወቅ ገልጸው ነበር።

በምርጫ 97 ኢህአዴግ መሸነፉን ተከትሎ በአዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙ ባዶ ቦታዎች በአቶ መለስ ዜናዊ ትእዛዝ ተመዝግበው ከህወሃት ጋር ግንኙነት ላላቸው የአንድ አካባቢ ሰዎች እንዲሰጥ መደረጉን አቶ ኤርምያስ አክለው ገልጸዋል።

በሌላ ዜና ደግሞ የአዲስ አበባ መስተዳድር በ40 በ60 እና በ20 በ80 የኮንዶሚኒየም ቤት መርሃ ግብሩ ከ800 ሺ በላይ ነዋሪዎችን ቢመዘግብም እስካሁን ድረስ ያሰራው ከ1 ሺ 300 አለመብለጡ ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ ቀድሞ ከተገመተውም በላይ በርካታ አመታትን እንደሚወስድ ታውቋል።

በእየአመቱ 50 ሺ ቤቶች ቢሰሩ እስካሁን የተመዘገቡትን የቤት ባለቤት ለማድረግ ከ16 አመታት በላይ እንደሚወሰድ መረጃዎችን ዋቢ አድርጎ ኢሳት ሲዘግብ ቢቆይም፣ አሁን በሚታየው አሰራር ዜጎች የቤት ባለቤት ለመሆን በርካታ አመታትን ለመጠበቅ ይገደዳሉ።

መስተዳድሩን ከገጠሙት ችግሮች መካከል አንዱ የመሬት አቅርቦት እጥረት ሲሆን፣ የኦሮምያ ልዩ ዞኖችን ከህዝብ ፈቃድ ውጭ በጉልበት ወደ አዲስ አበባ ማስገባት ካልተቻለ የኮንዶሚኒየሙ ፕሮጀክት ተግባራዊ እንደማይሆን ምንጮች ይናገራሉ።