አቶ ገብረመድህን አርአያ የዘማናችን አሉላ አባ ነጋ ተብለው በከፍተኛ ክብር ተሰየሙ

ሰኔ ፲፱ (አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በምእራብ አውስትራሊያ በፐርዝ ከተማና አካባቢዋ ኗሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ጁን 23 ቀን 2013 ባደረጉት ልዩ ዝግጅት ታዋቂውን የነፃነት ተፋላሚና የቁርጥ ቀን የኢትዮጵያ ልጅ አቶ ገብረመድህን አርአያን የዘመናችን አሉላ አባ ነጋ በማለት በክብር ሰየሙዋቸው።

በዚህ ለእርሳቸው ታስቦ በተደረገው ልዩ የእራት ግብዣ ስነ ስርዓት ላይ በርካታ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያን የተገኙ ሲሆን፣ እንግዶቹ ለአቶ ገብረመድህን አርአያ ያላቸውን ልዩ ክብርና አድናቆት በየተራ እየተነሱ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

 

በዚሁ መሰረትም አቶ ገብረመድህን ህወሓት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ይዞ የተነሳውን እኩይ አላማና ተግባር በማጋለጥ ያደረጉት ጉልህ አስተዋጽኦ፣ በተለያዩ የሚዲያ ዘርፎች በመረጃ የተደገፉ መግለጫዎችን እና ትምህርቶችን በመስጠት የከወኗቸው ሥራዎች፤ እንዲሁም ለእሩብ ምእተዓመታት ያህል በጽኑነት፤ በቆራጥነትና በሕዝብ ወገናዊነት መቆማቸው በምሳሌነት በጉልህ ተጠቅሰዋል።

ለአቶ ገብረመድህን ማህበረሰቡ በጋራ ባዘጋጀው በዚሁ ስነስርዓት ላይ በአረንጓዴ፤ ቢጫና ቀይ ቀለማት በደመቀ የኢትዮጵያ ሙሉ ካርታ ላይ የጀግናው ራስ አሉላ አባነጋ ምስል የተቀመጠበት የታሪክ ማስታወሻ ከታላቅ አክብሮት ጋር ተበርክቶላቸዋል። እንዲሁም ግለሰቦች በራሳቸው አነሳሽነት ያዘጋጁላቸው የተለያዩ ሽልማቶች ተበርክተውላቸዋል።

በዚሁ ደማቅ ስነስርዓት ላይ አቶ ገብረመድህን ባደረጉት ንግግር ለሳቸው ተብሎ የተደረገውን ይህን ታላቅ ዝግጅት ያልጠበቁት እንደነበር ገልጸው ለዚህ ክብር ያበቃቸውን ወገናቸውን እጅግ አድርገው እንደሚወዱ፣ እንባ እየተናነቃቸው የታዳሚውን ስሜት በጥልቅ በሚነካ አኳኋን ገልጸዋል።

ይህ ለርሳቸው የተደረገው የክብር ዝግጅት የበለጠ ለወገናቸውና ለሃገራቸው ሌት ተቀን ተግተው እስከመጨረሻው ለመታገል ብርታት እንደሚሰጣቸውም ተናግረዋል።

እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በርትቶ በመታገል የዜግነት ግዴታውን እንዲወጣ በአጽንኦት አሳስበዋል።

“አገራችን የጋራ ናት፣ በመሆኑም ችግሩ የጋራችን ነው፣ እንዲያ በመሆኑም የጋራ መፍትሄ ያስፈልገዋል” በማለት ወያኔን ከስሩ ነቅለን እስካልጣልነው ድረስ በጥገናዊ እርምጃ መፍትሄ የማይገኝ መሆኑን አቶ ገብረመድህን አስገንዝበዋል።

 

ህወሓት ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ቀላሉ ዘዴ አማራውን ማጥፋት ነው በሚለው እስትታተጂው ገፍቶ እንደቀጠለበት በገሃድ እየታየ መሆኑን የተለያዩ መረጃዎች እንደሚያረጋግጡም አስገንዝበዋል።

 

ታዳሚው በበኩሉ ለአቶ ገብረመድህን ያለውን አድናቆት ከምግለጹም በተጨማሪ፣ የሳቸውን ጥሪ እንደተቀበለው ኢትዮጵያዊ ወኔ በተሞላበት ስሜት አረጋግጧል። እኚህን የኢትዮጵያዊ አርበኝነት ምሳሌ የሆኑትን ጀግና አቅፎና ደግፎ እስከመጨረሻው እንደሚንከባከባቸውም ታዳሚው ገልጿል።

በመጨረሻም ታዳሚው ለአቶ ገብረመድህን አርአያ የሚመኝላቸው ብዙ መስዋእትነት የከፈሉላትን እና የሚወዷትን የእናት ሃገራቸውን የኢትዮጵያን ትንሳኤ ከሕዝቡ ጋር በጋራ ድል ለማየት የሚያበቃ ረጅም እድሜና ጤንነት ፈጣሪ እንዲያድላቸው መሆኑን በከፍተኛ ስሜት ገልጿል።