አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ  ከስድስት ወራት በሁዋላ  ለመጀመሪያ ጊዜ ልጆቻቸውን ጨምሮ ከቤተሰቦቻቸው ጋር  በስልክ መነጋረራቸው ተስፋ እንደሰጣቸው ባለቤታቸው ወይዘሮ የምስራች ገለጹ።

ጥር ፲፩(አስራ አንድ ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ወይዘሮ የምስራች በተለይ ለኢሳት  ሲናገሩ፤ አቶ አንዳርጋቸው ካልታወቀ እስር ቤት ሆነው ልጆቻቸውንና የቤተሰቡን አባላት ድንገት ሲያናግሩ ደንግጠው እንደነበር በመጥቀስ፤ ድንገት የተደወለውን ስልክ ሲያነሱ በድምጻቸው ወዲያው እንደለዩዋቸው ግልጸዋል።

ሰላምታ ከተለዋወጡ በሁዋላ ጤንነታቸውን በተመለከተ እንደተጠያየቁና   አቶ አንዳርጋቸው በደህና ጤንነት ላይ መሆናቸውን እንደገለጹላቸውም ወዘይሮ የምስራች ተናግረዋል።

<<ድምጹን ሥንሰማው  ደስታም፣ድንጋጤም የተቀላቀለበት ፤ እንዲሁም ምንም ልናደርግለት ባለመቻላችን  ቁጭት፣ንዴት እና አቅም የመጣት ስሜት ተሰማን >> ሲሉም ወይሮ የምስራች በሀዘን ተውጠው ገልጸዋል።

በሚቀጥለው ወር የእንግሊዝ  የፓርላማ አባላትና የጠበቆች ማህበር ተወካዮች  አቶ  አንዳርጋቸውን ለማዬትና ለማስፈታት ወደ ኢትዮጵያ እንደሚያቀኑ ሐሙስ እለት <<ኢንዲፐንደንት>> አስነብቧል።

 አቶ አንዳርጋቸው ከቤተሰቦቻቸው ጋር መነጋገራቸውን ተከትሎ የምክር ቤት አባላትና የጠበቆች ማህበር ተወካይ ወደ ኢትዮጵያ ማቅናታቸው ተስፋ እንዳሳደረባቸውም ወይዘሮ የምስራች ተናግረዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ አቶ አንዳርጋቸው ከስድስት ወራት በሁዋላ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ  በስልክ መነጋገራቸውን የሰሙ በርካታ ኢትዮጵያውን ወደ ኢሳት ስልክ በመደወል ደስታቸውን የገለጹ ሲሆን፤ “ክስተቱ የጀመርነውን ትግል አጠናክረን እንድንቀጥል የሚያበረታታን ነው”ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።