አቶ አብርሃ ደስታ ህይወቱን ያተረፉትን የመቀሌ ወጣቶችን አመሰገነ

ኢሳት (ሰኔ 6 ፥ 2009)

ባለፈው ቅዳሜ በመቀሌ ከተማ ድብደባ የተፈጸመበት አቶ አብርሃ ደስታ ህይወቱን ያተረፉት የመቀሌ ወጣቶች መሆናቸውን ገለጸ። የአረና ፓርቲ ሊቀመንበር የሆነው አቶ አብርሃ ደስታ ቅዳሜ ሰኔ 3 ቀን 2009 አም ምሽት በመቀሌ ከተማ ባልታወቁ ሃይሎች በተፈጸመበት ጥቃት ከፍተኛ ጥቃት እንደደረሰበትም ተመልክቷል። 

አቶ አብርሃ ደስታ ቅዳሜ ምሽት ከምሽቱ 1 ሰዓት ተኩል ላይ በመቀሌ ከተማ አብርሃ ካስል በተባለው አካባቢ ጥቃቱን የፈጸሙበት ሶስት ሰዎች እንደሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ህይወቱን የታደጉት በአካባቢው ሲያልፉ የነበሩ የባጃጅ ተሽከርካሪ ሹፌዎች መሆናቸውም ተመልክቷል። ከጥቃቱ ሶስት ቀን በኋላ ማክሰኞ ዕለት አቶ አብርሃ ደስታ በማህበራዊ ገጹ ላይ ባሰፈረው መልዕክት “የመቀሌ ወጣቶች ባይደርሱልኝ ኖሮ ሟች ነበርኩኝ” ሲል የታደጉትን አመስግኗል።

ሁለት ሰዎችን  ሸኝቶ ሲመለስ ጥቃት እንደተፈጸመበት የተገለጸው የአረና ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ አብርሃ ደስታ የኪስ ቦርሳውንና የእጅ ስልኩን ጨምሮ ንብረቶችን በደብዳቢዎቹ እንደተወሰደበት ተመልክቷል። ጥቃቱን ማን ለምን ዓላማ እንዳደረሰው የታወቀ ነገር ባይኖርም፣ የአረና ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ለዜና ሰዎች እንደገለጹት ጥቃቱ ተራ ወንጀል ሳይሆን፣ ፖለቲካዊ አላማ ያለው ነው።

አቶ አብርሃ ደስታ ቀደም ሲል በተመሰረበት ክስ በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ተይዞ እንደሚቀርብ ውሳኔ መተላለፉም ይታወሳል። ውሳኔውም ሳምንታትን እንዳስቆጠረ ይታወቃል።