በትግራይ አድዋ ከተማ የሚኖሩ ሙስሊሞች ጫና እየተደረገባቸው ነው ተባለ

ኢሳት (ሰኔ 6 ፥ 2009)

በትግራይ ክልል አድዋ ከተማ የሚኖሩ ሙስሊሞች መስጊድ ገብተን ለመጸለይ እንዲሁም ሌሎች ሃይማኖታዊ ግዴታቸውን እንዳይወጡ ጫና እየተደረገባቸው መሆኑን ገለጹ። የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን የመብት ጥያቄ ደግፈውታል በሚል ወከባ እየደረሰባቸው ያሉ ሙስሊሞች በቁጥር ከ150 እንደሚበልጡም ተመልክቷል።

ሰለባዎቹ ለኢሳት እንደተናገሩት ይቅርታ ካልጠየቃችሁ ወደ መስጊድ አትገቡም ከሚለው ተፅዕኖ ባሻገር የሙስሊሞችን የመብት ጥያቄ ደግፋችኋል በሚል ፍ/ቤት ቀርበው ገንዘም ተቀጥተዋል። በረመዳን ወቅት መስጊድ ገብተን ጸሎት እንዳናደርስ ተከልክለናል በማለት ምሬታቸውን የገለጹት ወገኖች የኢትዮጵያ ሆነ የአለም ህዝብ ከጎናቸው እንዲሆነ ጥሪ አቅርበዋል።

ወንጀላችንን ዕምነታችንን አክብረን መያዛችን እንጂ ምንም የፈጸምነው ወንጀል የለም የሚሉት በአድዋ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ሙስሊሞች፣ የምታራምዱት የዋህቢያ ዕምነት ስለሆነ ይህንን ካልተዋችሁ በሚል ከ2003 ጀምሮ የቀጠለው መከራ እየተጠናከረ መቀጠሉን አስረድተዋል።