(ኢሳት ዲሲ–ሐምሌ 27/2010) በቅርቡ ሕይወታቸው ያለፈውን የብአዴን አመራር አቶ ተስፋዬ ጌታቸውን ቤተሰቦች ለመደገፍ ባለሃብቶች የ25 ሚሊየን ብር ስጦታ ማድረጋቸው ታወቀ።
አቶ ተስፋዬ ጌታቸው በኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው የለውጥ እንቅስቃሴ በብአዴን በኩል ካሉ ግንባር ቀደሞች አንዱ መሆናቸውም ተመልክቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በሎስ አንጀለስ ከኢትዮጵያውያን ጋር ባካሄዱት ውይይት አቶ ተስፋዬ ጌታቸውን በስም ጠቅሰው አስተዋጿቸው የጎላ እንደነበር መስክረዋል።
የብአዴን የኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት አማካሪ እንዲሁም የብአዴን ጽሕፈት ቤት ሃላፊ የነበሩት አቶ ተስፋዬ ጌታቸው ሐምሌ 18/2010 በአሜሪካ ጆርጅ ዋሽንግተን ሆስፒታል ሕይወታቸው አልፏል።
ለሕክምና ወደ አሜሪካ ከተጓዙ ወራት ያስቆጠሩት አቶ ተስፋዬ ጌታቸው ኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ያለውን ለውጥ በተመለከተ በዋሽንግተን ዲሲና አካባቢዋ ከሚገኙ አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ጋር ሲወያዩና ለለውጡ ድጋፍ እንዲያደርጉ ሲቀሰቅሱ መቆየታቸውም ተመልክቷል።
የተካሄደውን የለውጥ እንቅስቃሴ በማስረዳትም ስለለውጥ ሒደቱ ከፍተኛ ግንዛቤ ማስጨበጣቸውንም መገንዘብ ተችሏል።
አቶ ተስፋዬ ጌታቸው ለሕክምና አሜሪካ ለወራት ቢቆዩም ሕክምናው ባለመሳካቱ በኦፕራሲዮን ላይ እያሉ ሕይወታቸው አልፏል።
ሐምሌ 18/2010 በዋሽንግተን ዲሲ ሕይወታቸው ያለፈው አቶ ተስፋዬ ጌታቸው አስከሬናቸው ወደ ኢትዮጵያ ተልኮ የቀብራቸው ስነስርአትም በባህርዳር ከተማ ተፈጽሟል።
የአቶ ተስፋዬ ጌታቸው ቤተሰብን ለመርዳት በስታር ቢዝነስ ግሩፕ ባለቤት በአቶ አበባው ደስታ አስተባባሪነት የ25 ሚሊየን ብር እርዳታ መገኘቱም ተመልክቷል።
የ25 ሚሊየን ብሩን ድጋፍ ያደረጉት የአማራ ክልል ባለሃብቶች መሆናቸውም ተመልክቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አቶ ተስፋዬ ጌታቸው በለውጥ ሒደቱ ውስጥ ከፍተኛ ሚና እንደነበራቸው በቅርቡ ሎስአንጀለስ በነበረው መድረክ ላይ ተገልጿል።