አቶ በረከት ስምዖን ”የሁለት ምርጫዎች ወግ‘ በሚል ምርጫ 1997 ዓ/ም እና 2002 ዓ/ም አነፃጽረው የጻፉት መጽሐፍ ማክሰኞ ይመረቃል

08 ቀን 2004 /

ኢሳት ዜና:-የአቶ መለስ ቀኝ እጅ የሚባሉት የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚንስትር አቶ በረከት ስምዖን ”የሁለት ምርጫዎች ወግ‘ በሚል ምርጫ 19 97 ዓ.ም እና 2002 ዓ.ም አነፃጽረው የጻፉት መጽሐፍ ማክሰኞ በሸራተን አዲስ ላሊበላ አዳራሽ ይመረቃል፡፡

የክብር እንግዶች የሆኑ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት፣ የዩኒቨርስቲ ምሁራን ይበልጡኑ የስነጽሑፍና የታሪክ ምሑራን እና የሀገር ውስጥና የውጭ አገር ጋዜጠኞች ተለይተው ተጋብዘዋል፡፡

አቶ በረከት በመጸሐፉ ላይ የሁለቱን ምርጫዎች ተመሳሳይነትና ተቃርኖ ያቀረቡ ሲሆን ፣ “በ1997 ዓ.ም ምርጫ በከተሞች አካባቢ ተቃዋሚዎች ንፋስ አመጣሽ ድምጽ አጋጥሟቸው ነበር፣ ይህም ሁኔታ በሰላም የተጀመረውን ሁኔታ በብጥብጥ እንዲቋጭ አድርጎታል” ይላሉ።

የምርጫ 2002 ዓ.ም ጅምርና ፍጻሜን በሰላም ተጀምሮ በሠላም የተጠናቀቀ ነው በማለት ያወደሱት አቶ በረከት፣  ኢህአዴግ ከስህተቶቹ የተማረ ፓርቲና የሕዝብን ይሁንታ አጥለቅልቆ ያገኘ ነው ይላሉ፡፡

በ19 97 ምርጫ  ተቃዋሚዎች ቀደም ሲል ከነበራቸው 12 የፓርላማ ወንበር ወደ 170 የተመነደጉበት ነበር ሲሉ በመጽሐፋቸው የገለጹት አቶ በረከት፣  በ2002 ዓ.ም ምርጫ ቁልቁል ሄደው ወደ 1 የፓርላማ ወንበር ያሽቆለቆሉበት ና ሕዝቡ ድጋፉን ለኢህአዴግ የመለሰበት ነው ሲሉ ይደመድማሉ፡፡

ሪፖርተራችን ያናገራቸው አንድ የሲቭል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ የቋንቋእና ፍልስፍና ምሑር እንደገለጹት አቶ በረከት ይሄን መጽሐፍ ለመጻፍ ካሰቡ መቆየታቸውን መረጃ እንዳላቸው ገልጸው፣  ለዚህም ሲባል ከአደባባይ ገለል ብለው ሲሰሩና ረቂቁንም ለአቶ መለስና ለአቶ ስብሃት ነጋ እያስነበቡ እያሻሻሉ ነው የቆዩት በማለት ገልጠዋል።

መጽሐፉ አቶ በረከት ስምዖን የማስታወቂያ ሚንስትር አጋፋሪ ሆነው በሚሰሩበት ጊዜያት ያን አይነት የተበላሸ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ በኢህአዴግ መሰራቱ እና ሽንፈት ማጋጠሙ በእርሳቸውና በፓርቲያቸው ላይ የሥነ-ልቦና ጠባሳ (ትራውማ) በማሳረፉ ይህ መጽሐፍ ለእርሳቸውና ለፓርቲያቸው ማገገሚያ ፍቱን መድሃኒት ተደርጎ ታስቧል ብለዋል፡፡