አዲሱ ሊዝ አዋጅ ከንግድ ማህበረሰቡ ከፍተኛ ተቃውሞ ገጠመው

08 ቀን 2004 /

ኢሳት ዜና:-የንግዱን ማህበረሰብና ተቃውሞ አስመልክቶ ምላሽ ይሰጣሉ ተብለው በስብሰባው የተጋበዙት የመንግስት ባለስልጣን ሳይገኙ ቀሩ።

በሁኔታው ቅር የተሰኙት የንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ በበኩላቸው፦”ጥያቄዎችማ አሉን፤ የሚመልስልን አጣን እንጂ” በማለት መንግስት  የንግድ ማህበረሰቡ ጥያቄዎችና ቅሬታዎች ሊፈታ እንዳልቻለ ጠቁመዋል።

ባለፈው ዓርብ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ባዘጋጀው ሁለተኛው አዲስ ቻምበር ቢዝነስ ፎረም አጀንዳ ሆነው የቀረቡት ሁለት ነጥቦች የአምስት ዓመቱ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድና አዲሱ የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ የወጣው አዋጅ ናቸው።

 በሒልተን ሆቴል በተካሄደው በዚህ ውይይት የአምስት ዓመቱ ዕቅድ በተለይ  በሁለተኛ ደረጃ አጀንዳ ሆኖ የቀረበው  አዲሱ የሊዝ አዋጅ  ሙሉ በሙሉ ሊባል የሚችል ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡

እንደ ሪፖርተር ዘገባ፤የተሰብሳቢዎቹ የወቅቱ ትልቅ አጀንዳ ‹‹የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ›› የሚለው ይኸው አዲሱ የሊዝ አዋጅ የነበረ ሲሆን፤ ካለመንግሥት ተወካዮች ተሳትፎ ብቻቸውን ተወያይተው በተቃውሞ ተበትነዋል፡፡

ያለመንግስት ተወካዮች ተሳትፎ በተቃውሞ ሊበተን የቻለውም፤ በስብሰባው የተጋበዙት የመንግስት ባለስልጣን ሊገኙ ባለመቻላቸው ነው።

 በአዋጁ ላይ መግለጫ የሰጡት፤ የሕግ ባለሙያው አቶ አብዱ አሊ ሲሆኑ፤እንደ እርሳቸው ማብራሪያ  በተለይ አዲሱ የሊዝ አዋጅ ፤ሦስት ዋና ችግሮች አሉበት፡፡

 “የመጀመርያው ሕገ መንግሥቱ መሬት አይሸጥም አይለወጥም ቢልም፣ አዲሱ የሊዝ አዋጅ በመግቢያው ምቹ የመሬትና የመሬት ነክ ገበያ መኖር እንዳለበት ይገልጻል” ያሉት አቶ አብዱ፤ “ መሬት በሕገ መንግሥቱ የማይሸጥ የማይለወጥ ነው  እየተባለ  ምን ገበያ አለው? ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

 አዲሱ የሊዝ አዋጅ ከዚህም በላይ  መሬት የማግኘትን መብትና ከባንኮችም ብድር የማግኘት ሁኔታን እንደሚያጣብብ አቶ አብዱ አስረድተዋል።

አዋጁ  የሊዝ መብትን ስለማስያዝና ስለማስተላለፍ በሚደነግገው ክፍሉም፦” የሊዝ መብትን በዋስትና ያስያዘ ሰው፣ የዋስትና ግዴታውን ባለመወጣቱ በዋስትና መያዥያው ላይ የዕዳ ጥያቄ ከቀረበ- መሬትን የሚያስተዳድረው አካል የሊዝ ውሉን አቋርጦ መሬቱን በመረከብ፣ በአዋጁ መሠረት ገንዘቡን አስልቶ ቀሪውን ለሦስተኛ ባለመብቱ (ለባንክ) ይከፍላል፡፡ ትርፍ ገንዘብ ካለም፤ ለሊዝ ባለመብቱ ይመልሳል “ እንደሚል ያወሱት አቶ አብዱ፤ ‹‹የትኛው ባንክ ነው በዚህ ስሌት መሠረት የሚያበድረው?›› ሲሉ  በድጋሜ ጠይቃዋል።

” የዕድገትና ትራንስፎርሜሽኑን ዕቅድ ለማስፈጸም እነዚህ ግብዓቶች  መስተካከላቸው ወሳኝ አይደሉም ወይ? “ በማለት   አዋጁን  የሞገቱት  አቶ አብዱ ፤  “ቤት ተንቀሳቃሽ ንብረት ነው፡፡ ዋስትናም ነው፡፡ ቤት ሲሸጥ ከነመሬቱ  ጋር መሆን ይኖርበታል ፣ ይሁንና በአዲሱ የሊዝ አዋጅ ፦” ቤት ከተሠራ በኋላ መሬት የመንግሥት ነው፣ ቤቱ ግን የአንተ ነው” ማለት ምን ማለት ነው? ሲሉ ጥያቄያቸውን ይቀጥላሉ፡፡

የአቶ አብዱን  ጨምሮ የንግዱ ማኅበረሰብ ያነሳቸውን  ሌሎችም ተዛማጅነት ያላቸውን በርካታ ጥያቄዎች ይመልሳሉ ተብሎ ጥሪ የተደረገላቸው የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የመሬትና ማኔጅመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ እስራኤል ተስፋዬ፤ በስብሰባው ላይ ባለመገኘታቸው ጥያቄዎቹ ምላሽ ሳያገኙ ቀርተዋል፡፡
የሊዝ አዋጁን በሚመለከት በጊዜ እጥረት ምክንያት ጥያቄዎችን ማስተናገድ ያልቻሉት የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ፤ ‹‹ጥያቄማ አለን፤ መላሽ አጣን እንጂ፤›› ሲሉ ንግዱ ማህበረሰብ  በመንግስት  ላይ  ያለውን ቅሬታ ለማንጸባረቅ ሞክረዋል።

በስብሰባው ይገኛሉ ተብለው ሲጠበቁ የቀሩት አቶ እስራኤል፦” በስብሰባው ያልተገኘሁት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሌላ ስብሰባ ስለነበረኝ ነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

ባለስልጣኑ ይህን ፕሮግራማቸውን ጥሪ ላደረጉላቸው ለንግዱ ማህበረሰብ አካላት ቀደም ብለው ያሳውቁ፤አያሳውቁ የተገለጸ ነገር የለም።

የንግዱ ማኅበረሰብ ካነሳቸውና በአቶ አብዱ ሳይመለሱ ከቀሩ ጥያቄዎች መካከል፣ “አዋጁ” በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውይይት ሳይደረግበት፣ የንግድ ማኅበረሰቡም ሳይወያይበት መውጣቱ አግባብ አይደለም፡፡ ለምን ይህ ሆነ? ፕራይቬታይዜሽንና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ብዙ ድርጅቶችን ሸጦልናል፡፡ ሲሸጥልንም በሙሉ ክፍያ ሲሆን ፤ሊዝ የሚባል ነገር የለበትም፡፡ ያ  ውል አሁን እንዴት ሊሆን ነው? መንግሥት ሸጦልን ገንዘብ ከወሰደ በኋላ በሊዝ ነው ብሎ ተጨማሪ ገንዘብ ሊጠይቀን ነውን? ይህ አዋጅ መንግሥትንና ሕዝብን አይጥና ድመት የሚያደርግ ነው፡፡ መንግሥት ለምንድነው የንግዱ ማኅበረሰቡን ሊያድግ ሲል የሚጎሽመው?” የሚሉት ይገኙበታል፡፡
ይሁንና፤ ከመንግሥት በኩል መላሽ ባለመኖሩ የሊዝ አዋጁን በደፈናው በመቃወም ስብሰባው ተበትኗል፡፡