(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 24/2010)በቅርቡ ከፖሊሲ ምርምርና ጥናት ተቋም ምክትል ሃላፊነታቸው በፈቃዳቸው ስራቸውን የለቀቁት አቶ በረከት ስምኦን የሙስና ምርመራ እየተካሄደባቸው መሆኑን ምንጮች ለኢሳት ገለጹ።
በተለይም በ300 ሚሊየን ብር ወጪ ግንባታው በመጠናቀቅ ላይ ያለውና በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኘው ደብል ትሪ ባለ አራት ኮከብ ዘመናዊ ሆቴል የርሳቸውን ነው በሚል ምርመራ ተጀምሯል።
በአቶ በረከት ላይ የተጀመረው ምርመራ ሌሎች አሏቸው የተባሉና በግለሰቦች ስም የተያዙ ንብረቶችንም እንደሚጨምር ምንጮቹ ለኢሳት ገልጸዋል።
በሕዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ውስጥ በተፈጠረው ክፍፍል “የመለስ ሌጋሲ” የተባለውና በአቶ በረከት የሚደገፈው የእነ አቶ አባይ ወልዱ ቡድን እየተዳከመ መገኘቱን ተከትሎ ከንግድ ባንክ የቦርድ ሊቀመንበርነት ተባረዋል።
ይህን ተከትሎም የፖሊሲ ምርምር ተቋም ምክትል ዳይሬክተርነታቸውን በፈቃዳቸው የለቀቁት አቶ በረከት ስምኦን ለሕወሃት መዳከምና በሀገሪቱ ለቀጠለው ቀውስ በሌላኛው የህወሃት ቡድን ተጠያቂ ሲደርጉ ቆይተዋል።
አሁን በአቶ በረከት ላይ የሙስና ምርመራ የከፈተውም ይህው ቡድን እንደሆነም መረዳት ተችሏል።
በዚህም አቶ በረከት በቤተሰቦቻቸውና በሌሎች ግለሰቦች ስም የሚያንቀሳቅሷቸው ተቋማት ተለይተው እንደታወቁ ምርመራ ተጀምሯል።
ጄ ኤ ኤፍ ቢ ቢ በተባለ ኩባንያ ስም የተገነባውና ግንባታው እየተጠናቀቀ የሚገኘው ባለ 11 ፎቁ ደብል ትሪ ሆቴል ቅድሚያ ትኩረት ውስጥ መግባቱ ተመልክቷል።
ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ አካባቢ የተገነባውና 106 መኝታ ክፍሎች ያሉት ይህ ሆቴል በባለቤትነት የተመዘገበው አቶ ተካ አስፋው በተባለ ግለሰብና በቤተሰባቸው እንደሆነም ታውቋል።
ሆቴሉ 70 በመቶ በአቶ ተካ አስፋው እንዲሁም 30 በመቶ በባለቤታቸው በወይዘሮ ፍቅረማርያም በላይ መያዙንና በሰነዶች መመዝገቡን ምንጮቹ ይገልጻሉ።
ምርመራው በግለሰቦቹ የሃብት ምንጭና በአቶ በረከት ስምኦን ግንኙነት ዙሪያ የሚያተኩር እንደሆነም ከመረጃው ለማወቅ ተችሏል።
የሆቴሉ ባለቤት ሆነው የተመዘገቡት አቶ ተካ አስፋው ረዳት አቃቢ ህግ ሆነው በህግ ሙያ ውስጥ የቆዩ መሆናቸው ታውቋል።
በሼህ መሀመድ አላሙዲን ኩባንያዎች ውስጥ አሁን በህግ አማካሪነት እየሰሩ መሆናቸው የተነገረው አቶ ተካ አስፋው፣ከአቶ በረከት ስምኦን ጋር ያላቸው ግንኙነት በሼህ መሀመድ አላሙዲን አማካኝነት እንደሆነም የምርመራውን ፍንጮች መሰረት ያደረጉት የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
አቶ በረከት ስምኦን ከደብል ትሪ ሆቴል በተጨማሪ በባለቤታቸው ስም አለ የተባለውን ማተሚያ ቤት ጨምሮ በሌሎች በዘረፋ ተገነቡ በተባሉ ድርጅቶቻቸው ላይ መርመራው እንደሚቀጥልም መረዳት ተችሏል።
በሕዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ውስጥ ያለው የሃይል አሰላለፍ አሁን ባለበት በእነ አቶ ስብሃት የበላይነት ከቀጠለና ሰራዊቱንም ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር ከቻሉ በሌሎች የብአዴን መሪዎች እንዲሁም በኦህዴድ መሪዎች በእነ አቶ አባዱላ ገመዳ ላይ ተመሳሳይ ሁኔታዎች እንደሚቀጥሉ የቅርብ ምንጮቹ ይገልጻሉ።
በአለም አቀፉ ሂልተን ሆቴል መለያ የሚታወቀውና በአዲስ አበባ ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አካባቢ የተገነባው ሆቴል ከ6 ወራት በኋላ በሰኔ ወር ስራ ለማስጀመር መርሃ ግብር የተያዘ ቢሆንም በአቶ በረከት ላይ የተጀመረው ምርመራ በሆቴሉ ስራ መጀመር ላይ ምን እንደሚያስከትል ግን የታወቀ ነገር የለም።