በኮሬና ጉጂ የኦሮሞ ብሄር ተወላጆች መካከል ተከስቶ የነበረው ግጭት መቀጠሉ ተሰማ

(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 24/2010)በኮሬና ጉጂ የኦሮሞ ብሄር ተወላጆች መካከል ተከስቶ የነበረው ግጭት መቀጠሉ ተነገረ።

የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት በደቡብና ኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ ድንበሮች በወሰን ማካለል ሰበብ የአካባቢው ባለስልጣናት ያቀናበሯቸው ግጭቶች ለአያሌ ዜጎች ሞትና መፈናቀል ምክንያት ሆኗል።

በደቡብ ኮሬና በጉጂ ኦሮሞዎች መካከል በተከሰተው ግጭት ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉ የአካባቢው ነዋሪዎች ለከፍተኛ ስቃይና ችግር መዳረጋቸውን ምንጮቻችን ገልጸዋል።

የአካባቢው ምንጮች እንደሚሉት ለዘመናት ተከባብረው፣ተዋደውና ተዋልደው ይኖሩ የነበሩት እነዚሁ ብሔረሰቦች በባለስልጣናት ልዩ ትዕዛዝ በቡሌ ሆራና ሻኪሶ አካባቢ ከነበሩበት ቀዬ ተፈናቅለዋል።–ንብረታቸውንም ተዘርፈዋል።

ከተፈናቃዮቹ መካከልም ታዳጊ ህጻናት፣ነፍሰጡሮች፣የሚያጠቡ እናቶችና አቅመ ደካማ አዛውንቶች እንደሚገኙበት የአይን እማኞች ገልጸዋል።

እስካሁ ድረስም ተፈናቃዮቹን ወደ ቀያቸው የመመለስም ሆነ በተጠለሉበት ጣቢያቸው በቂ እርዳታ እየተደረገላቸው አለመሆኑ ታውቋል።

ችግራቸውን ለደቡብ ክልል መስተዳድር አቤቱታ ቢያቀርቡም እስካሁን ምላሽ እንዳላገኙም ነው የተነገረው።

እንዲያውም ችግሩን ለመሸፋፈን እየሞከሩ ይገኛሉ ብለዋል።

የደቡብ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ደሴ ዳልኬ በከፍተኛ ጦር ታጅበው ወደ አካባቢው ከመጡ በኋላ ሰላማዊ ወረዳዎችን ጎብኝተው ተፈናቃዮችን ሳያዩ መመለሳቸውም ብዙዎችን አሳዝኗል ነው ያሉት።

በቡሌ ሆራና ሻኪሶ አካባቢ በተለይ ካለፉት አራት ወራት ወዲህ ሲካሄዱ የነበሩ ግጭቶችንና ጥቃቶችን ኢሳት ሲዘግብ መቆየቱ ይታወሳል።