አቶ በረከት ስምኦን ማንኛውንም ጣቢያ ልንታገስ እንችላለን በኢሳት ጉዳይ ግን አንደራደርም አሉ

ሰኔ ፱ (ዘጠኝ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ከጥቂት ሳምንታት በፊት በአቶ በረከት ስምኦን የሚመራው የኢትዮጵያ የልኡካን ቡድን ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ የሚተላለፈውን የኤርትራ የቴሌቪዥን ጣቢያ ከእንግዲህ እንደማያፍን በጽሁፍ ለአረብሳት ባለስልጣናት ማረጋገጫ መስጠቱን መዘገባችን ይታወሳል። የኢትዮጵያ መንግስት ለአረብሳት ባለስልጣናት እንደገለጠው የኤርትራ መንግስት ወደ ኢትዮጵያ የሚያሰራጨውን የተቃዋሚዎች ልሳንና እንዲሁም ከኢሳት እየወሰደ የሚያስተላለፈውን ማንኛውንም ዝግጅት  የሚያቋርጥ ከሆነ፣ የኢትዮጵያ መንግስትም በአገሩ ያሉ የኤርትራ ተቃዋሚዎች የሚያስተላልፉት ጸረ መንግስት ዝግጅቶች ለማቋረጥ ዝግጁ መሆኑን ይሁን እንጅ የኤርትራ መንግስት “ብትፈለጉ የ 1 ሰአቱን ዝግጅት ወደ 24 ሰአት ከፍ አድርጉት፣ በእኛ ቴሌቬዥን ጣቢያ ላይ የሚተላለፉትን ዝግጅቶች የኢትዮጵያ መንግስት አይወስንልንም” በማለት መልስ ሰጥቶ ነበር።

የአረብሳት ባለስልጣናትን ሲለምን የቆየው የኢትዮጵያ መንግስት በመጨረሻም ከአሁን በሁዋላ የኤርትራን ቴሌቪዥን እንደማያፍን ግዴታ በመግባቱ ተቋርጦ የነበረው በአረብሳት የሚተላለፈው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እንደገና ስራ እንዲጀምር ተፈቅዶለታል።  በአቶ በረከት የተመራው የልኡካን ቡድንን እንቅስቃሴ በቅርበት የተከታተሉ አንድ ስማቸው እንዳይገለጥ የፈለጉ ከፍተኛ ባለስልጣናን በቅርቡ በኢሳት የቀረበውን ዘገባ ከተከታተሉ በሁዋላ በድርድሩ ወቅት  የተነሱትን ነጥቦች አካፍለውናል።

አቶ በረከት በድርድሩ ወቅት ደጋግመው ያነሱ የነበረው ስለ ኢሳት ነው። ኢሳት በአረብሳት ተመልሶ የሚመጣ ከሆነ የኢትዮጵያ መንግስት ህልውናውንና ብሄራዊ ደህንነቱን ለማስከበር ሲል ማንኛውንም እርምጃ ለመውሰድ ይገደዳል በማለት  ተናግረዋል። የኤርትራን ቴሌቪዥንን ልንታገስ እንችላለን ኢሳት ግን ሙሉ በሙሉ በፓርላማ አሻባሪ ከተባሉት ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነው የግንቦት 7 ልሳን በመሆኑና፣ በህዝብ መካከል እልቅቲት ለመፍጠር 24 ሰአት የሚሰራ፣ ለኢትዮጵያ መንግስትና ለህዝቦቿ አስጊ የሆነ የቴሌቪዥን ጣቢያ በመሆኑ መንግስት ራሱን ለመከላከል አስፈላጊውን እርምጃ ቢወስድ ተጠያቄ አይሆንም ሲሉ አቶ በረከት ለአረብሳት ባለስልጣናት ገልጠዋል።

የአረብሳት ባለስልጣናትም እኛ የትኛውን ጣቢያ ማስተላለፍ እንዳለብንና እንደሌለብን የመወሰን መብት አለን፣ የኢትዮጵያ መንግስት ሊወስንልን አይገባም በማለት መልስ ሲሰጡ አቶ በረከት ሳምሶናይታቸውን ከፍተው የኢሳትን ዝግጅቶች አስተርጉመን ይዘን የመጣን በመሆኑ እራሳችሁ ተመልክታችሁ መፍረድ ትችላላችሁ በማለት ፊልሞችን አቅርበዋል። የአረብሳት ባለስልጣናት በበኩላቸው እኛ ይህን ሁሉ ፊልም ለማየት ጊዜው የለንም በማለት መልስ ሰጥተዋል። አቶ በረከት ለአረብሳት ባለስልጣናት በእንግሊዝኛ አስተርጉመው ካቀረቡዋቸው ፊልሞች መካከል ከአባ ኒቆዲሞስ አስፋው ጋር የተደረገው ቃለምልልስ ጨምሮ ሌሎች በርካታ ቃለምልልሶች ይገኙበታል።

የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ንግግር ያስገረማቸው አንድ የአረብሳት ባለስልጣን ” አትዮጵያ በእነዚህ ሰዎች ነው የምትመራው? እጅግ ያሳፍራል” በማለት መናገራቸውን ምንጫችን ገልጠዋል።

ጉዳዩን በተመለከተ ኢሳት አንድ ከፍተኛ የአረብሳት ባለስልጣናትን አነጋግሮ ነበር። ባለስልጣኑ ስማቸው እንዳይነገር አሳስበው ” ኢሳት የአረብሳትና የኢትዮጵያ መንግስት የጦር አውድማ መሆኑን ባለስልጣኑ ገልጠዋል።

ባለስልጣኑ ” ለመሆኑ ምን አይነት ዝግጅቶችን ብታቀርቡ ነው የኢትዮጵያ መንግስት አሸባሪ በማለት የሚፈርጃችሁ ? የሚል ጥያቄ ለጋዜጠኛው  አቅርበውለታል። ኢትዮጵያ በምን አይነት ሰዎች እንድመትምራ ግንዛቤ ይዘናል የኢትዮጵያ መንግስት አምባገነን በመሆኑ ነጻ አመለካከትን እንደ ጦር እንደሚፈራ በመካከለኛው ምስራቅ እየሆነ ካለው ሁኔታ የምንመለከተው፣ እናንተ እነሱ እንደሚሉት ወንጀለኞች እንዳልሆናችሁ እናውቃለን፣ ያም ሆነ ይህ ኢሳትን ወደ አየር ለመመለስ ብዙ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንና የቴክኒክ አቋማችን መፈተሽ ስለሚኖርብን ጊዜ ልትሰጡን ይገባል ” በማለት የአረብሳቱ ባለስልጣን ተናግረዋል።

አልጀዚራ ወደ ኢትዮጵያ የሚያሰራጨው ዝግጅቱ በተደጋጋሚ እየታወከበት እንደሆነ በዚህም የተነሳ በተደጋጋሚ የስርጭት መስመሩን ለመቀየር መገደዱ ይታወሳል። አለማቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተንከባካቢ ድርጅት፣ የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት እና ሌሎችም አለማቀፍ ተቋማት የኢትዮጵያ መንግስት የመገናኛ ብዙህንን ለማፈን የሚያደርገውን ጥረት ሲያወግዙ ቆይተዋል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide