(ኢሳት ዲሲ–ነሐሴ 24/2010)ከብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት የታገዱትን አቶ በረከት ስምኦንና አቶ ታደሰ ካሳን ከድርጅቱ አመራሮች ጋር ለማስታረቅ እንቅስቃሴ የጀመሩ ባለሃብቶችና ፖለቲከኞች ተቃውሞ ገጠማቸው።
አቶ በረከትም ሆነ አቶ ታደሰ ካሳ በኢትዮጵያ ደረጃም ሆነ በአማራ ክልል ለፈጸሟቸው ወንጀሎች ለፍርድ እንዲቀርቡ ቢጠበቅም እናስታርቃለን የሚሉ የአማራ ክልል ባለሃብቶች እንቅስቃሴ መጀመራቸው ተቃውሞ እንደገጠመው ታውቋል።
እርቁ እንዲወርድ ባለሃብቶችን ይዘው እንቅስቃሴ የጀመሩት አቶ አዲሱ ለገሰና የተወሰኑ የጎንደርና የባህርዳር ባለሃብቶች ናቸው ተብሏል።
የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ነሐሴ 17ና 18/2010 አቶ በረከት ስምኦንና አቶ ታደሰን ለጊዜው ከአባልነት አግዷል።
በመጪው መስከረም አጋማሽ ይካሄዳል እስከተባለው የድርጅቱ ጉባኤ ድረስ የታገዱት ሁለቱ የብአዴን ነባር አመራሮች ከድርጅቱ አዲስ አመራሮችና ማዕከላዊ ኮሚቴው ጋር እሰጣ ገባ ውስጥ ገብተዋል።
በተለይም አቶ በረከት ስምኦን በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ወጥተው የብአዴን አመራሮችን ብቃት የላቸውም፣የስልጣን ጥመኞችም ናቸው ማለታቸው ውዝግቡን እንዲካረር አድርጎታል።
የብአዴን ጽሕፈት ቤት ሃላፊው አቶ ምግባሩ ከበደና የክልሉ ኮሚኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን የአቶ በረከትን ሃሳብ በማጣጣል የተባረሩት ሕግንና ደንብን መሰረት በማድረግ ነው ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም በብአዴን አመራሮች የተባረሩትን አቶ በረከትና አቶ ታደሰ ካሳን ከድርጅቱ አዲስ አመራሮች ጋር ለማስታረቅ የተወሰኑ የጎንደርና የባህርዳር ነጋዴዎች እንቅስቃሴ መጀመራቸው ታውቋል።
በብአዴን መስራችና ነባር አመራር አቶ አዲሱ ለገሰ አነሳሽነት የተጀመረው እንቅስቃሴ ከጎንደር 3 ነጋዴዎች ከባህርዳር ደግሞ ሁለት ነጋዴዎችን ያካተተ መሆኑ ነው የተነገረው።
እናም ይህን እንቅስቃሴ የተረዱት የአማራ ክልል ነዋሪዎች ነጋዴዎቹ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ያለበለዚያ ግን ሒደቱን ለማስቆም እንቅስቃሴና ትግል እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
ነዋሪዎቹ እንደሚሉት አቶ በረከት ስምኦንና አቶ ታደሰ ካሳ በአማራ ክልል ሕዝብም ሆነ በኢትዮጵያ ላይ ላደረሱት መጠነ ሰፊ ጥፋትና ወንጀል ለፍርድ መቅረብ አለባቸው።