ሰኔ ፲፮ (አስራ ስድስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሚኒስትር ዴኤታው ይህን ያሉት ትናንት በጽህፈት ቤታቸው በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ነው።
አቶ ሽመልስ በትናንቱ መግለጫቸው ትኩረት ያደረጉባቸው ሁለት ነጥቦች፦ በኦሞ ወንዝ አካባቢ እየተሰራ ያለውን የስኳር ፕሮጀክት አስመልክቶ ከሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እየተሰማ ያለውን ተቃውሞ እና መንግስት በ”ስካይፒ “፣ በ”ጎግል ቶክ” እና በ”ያሁ መሴንጄር” አማካይነት የሚደረጉ ጥሪዎችን ለማገድ ባወጣው አዋጅ ዙሪያ ከተለያዬ አቅጣጫዎች እየተሰነዘሩበት ያሉትን ትችቶች መሰረት ያደረጉ ናቸው።
ዓለማቀፉ የሰብዓዊ መብት ተቋማት ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ፤ በኦሞ ወንዝ ላይ እየተካሄደ ባለው የስኳር ልማት ፕሮጀክት በሺዎች የሚቆጠሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ከይዞታቸው መፈናቀላቸውን እና በአካባቢው የነበሩ የቱሪስት መስህቦች መውደማቸውን ተጨባጭ መረጃዎችን በመዘርዘር ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
ከሂዩማን ራይትስ ዎች በተጨማሪ በአካባቢና በተፈጥሮ ጥበቃ ላይ የሚንቀሳቀሱ አያሌ ድርጅቶች ተመሣሳይ ስጋት ሲገልጹ ቆይተዋል።
አቶ ሽመልስ ከማል ይህን የሂዩማን ራይትስ ዎች መግለጫ እና የብዙሀን ድርጅቶችን ስጋት እንደተለመደው ፦”መሰረት የሌለው ውሸት ነው” ሲሉ አጣጥለውታል።
“በእኛ እምነት ይህ ተቋም ከሰብዓዊ መብት ጉዳይ በዘለለ የርዕዮተ ዓለም አጀንዳ ያነገበ ድርጅት”ነው ሲሉም ሂዩማን ራይትስ ዎችን ዘልፈዋል-ሚኒስቴር ዴኤታው።
አያይዘውም፦”የስኳር ልማት ፕሮጀክቱ እየተካሄደ ያለው፤ የአካባቢውን ነዋሪዎች ተጠቃሚ ባደረገ መልኩ ነው “በማለት ተናግረዋል።
ይሁንና አቶ ሽመልስ በዚሁ መግለጫቸው 2000 ያህል የ አካባቢው ነዋሪዎች ከይዞታቸው እንደተፈናቀሉና በአራት መንደሮች እንደሰፈሩ ሲናገሩ ተደምጠዋል።
አክለውም፦“እነዚህ ነዋሪዎች ከይዞታቸው የተፈናቀሉት በፈቃዳቸው ነው” ብለዋል።
እጅግ በርካታ የ አካባቢው ነዋሪዎች ለዘመናት ከኖሩበት ቀያቸው በግዳጅ በመፈናቀላቸው ሳቢያ የድረሱልን ጥሪ እያሰሙ እና እያለቀሱ ለተለያዩ ዓለማቀፍ ተቋማት ብሶታቸውን እየገለፁ ባሉበት ጊዜ አቶ ሽመልስ ፦”ነዋሪዎቹ ከይዞታቸው የተፈናቀሉት በፈቃዳቸው ነው” ማለታቸው ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁትን ወገኖች ያሳዘነ ሆኗል።
አቶ ሽመልስ በግራ እና በቀኛቸው በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ እና በፕሬዚዳንት ግርማ ፎቶዎች ታጅበው በሰጡት በዚሁ መግለጫ ሌላው ያነሱት አወዛጋቢ ነጥብ፤ የኢትዮጵያ መንግስት የስካይፒ ጥሪንም ሆነ በጎግል እና በያሁ የሚደረጉ የድምጽ ጥሪዎችን በህግ አላገደም የሚለው ነው።
ኢትዮጵያ በቅርቡ ባወጣችው ህግ በስካይፒ፣ በያሁ መሴንጄር እና በጎግል ቶክ ጥሪ የሚያደርጉ ብቻ ሳይሆኑ የሚቀበሉ ጭምር እስከ 15 ዓመት በሚደርስ እስራት እንደሚቀጡ በግልጽ ሰፍሮ ይገኛል።
“ ለአገር ደህንነት “ በሚል ሰበብ የወጣው ይህ አዋጅ በይፋ መሰራጨቱን ተከትሎ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ከፍተኛ ተቃውሞዎችን እያስከተለ ይገኛል።
በአዋጁ ላይ ተቃውሞ የተነሳው ከውጪ አገር ተቋማት፣ ከፖለቲካ ድርጅቶች ፣ ከጋዜጠኞች እና ከነዋሪዎች ብቻ ሳይሆን በ ኢህአዴግ ውስጥ ጭምርም እንደሆነ የ ኢሳት ጠጨባጭ ምንጮች አረጋግጠዋል።
ተቃውሞው እጅግ ባየለበት ጊዜ አቶ ሽመልስ በጋዜጣዊ መግለጫ ፦”ህጉ የስካይፒ ጥሪዎችንም ሆነ የጎግል እና የ ያሁ አገልግሎቶችን የመገደብ ዓላማ የለውም። መንግስት ስካይፒን አግዷል እየተባለ የሚወራው ውሸት ነው” ሲሉ መደመጣቸው ብዙዎችን አስገርሟል።
ይሁንና አቶ ሽመልስ በደፈናው “ህጉ አያግድም” በማለት ለማስተባበል ከመሞከር ውጪ እንዴት እንደማያግድ ለማብራራት አልሞከሩም።
አቶ ሽመልስ፦“የአሜሪካን ድምጽ ራዲዮ ለምን ጃም አደረጋችሁ?” ተብለው ሲጠየቁ ፤ቪኦኤ በመንግስት ጃም እንዳልተደረገ የገለጹት፦መንግስታቸው ራዲዮን ጃም ለማድረግ ዲሞክራሲያዊ ባህርይው እንደማይፈቅድለት በመጥቀስ ነበር።
ሆኖም አቶ ሽመልስ ይህን ባሉ ማግስት አቶ መለስ በ አደባባይ ፦”ቪ ኦኤን ጃም ያደረግነው እኛ ነን” ማለታቸው ይታወሳል።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide