አቶ ማሙሸት አማረ በነፃ እንዲቀለቀቁ ፍርድ ቤቱ ወሰነ

ነኅሴ ፳፪ (ሀያ ሁለት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-አይሲስ ኢትዮጵያዊያንን በሊቢያ መግደሉን በመቃውሞ መንግስት በጠራው የሰላማዊ ሰልፍ ላይ ከለቅሶ ቤት ወደ ቤተ መንግስት የተደረገውን ሰልፍ አነሳስቷል በሚል ክስ የተመሰረተበት አቶ ማሙሸት አማረ በነፃ እንዲለቀቅ የአራዳ ፍርድ ቤት አራተኛ ወንጀል ችሎት ዛሬ ነሃሴ 22 ቀን 2007 ዓ.ም. ወስኗል፡፡
አቶ ማሙሸት አማረ ሚያዝያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም በተካሄደው ሰልፍ ላይ ሁከትና ብጥብጥ ፈጥሯል በሚል ተከሶ የነበር ቢሆንም በወቅቱ ከምርጫ ቦርድ ጋር በነበረው ክርክር ሰልፉ ላይ አለመገኘቱን የሚያረጋግጥ መረጃ በማምጣቱ በነፃ እንዲለቀቅ ተወስኖ ነበር፡፡ ነገር ግን ክሱ ወደማነሳሳት ተቀይሮ እስከ ዛሬ ድረስ እስር ቤት እንዲቆይ ተደርጓል፡፡
አቃቤ ህግ አቶ ማሙሸት ገንዘብ ከፍሎ ወጣቶችን ሰልፍ እንዳስወጣቸው፣ ወጣቶችን እንዳደራጀ፣ በሰላማዊ ሰልፉ ወቅትም መንግስትን የሚተቹ መፈክሮችን በመሪነት ሲያሰማ እንደነበርና ለሚያዝያ 14 ሰልፍም ሲያደራጅ እንደነበር ያስረዱልኛል ያላቸውን ሶስት የሰው ምስክሮችን ማሰማቱ ይታወሳል፡፡
ፍርድ ቤቱ የአቃቤ ህግ ምስክሮች የግል ሰራተኛ እንደሆኑ የምስክርነት ቃላቸውን ቢሰጡም፣ በመስቀለኛ ጥያቄ አንደኛው የመንግስት ሰራተኛ፣ ሁለተኛው የወጣቶች ሊግና የኢህአዴግ አባል፣ ሶስተኛው ደግሞ የጥቃቅንና አነስተኛ ባልደረባ መሆናቸውን በማመናቸው የሰጡት ምስክርነት ትክክል አለመሆኑን ያስረዳል፡፡ በተጨማሪም ምስክሮቹ ገዥው ፓርቲን የሚደግፉና የወጣት ሊግ አባል ሆነው ገዥው ፓርቲን የሚቃወም ግለሰብ ላይ የሰጡት ምስክርነት ገለልተኛ ነው ብሎ ለማመን ያስቸግራል ብሏል፡፡
የምስክሮቹ ቃል ታአማኒነት ስለሌለው አቶ ማሙሸት አማረ መከላከል ሳያስፈልገው በዛሬው ዕለት በነፃ እንዲለቀቅ ሲል ፍርድ ቤቱ መወሰኑን ነገረ ኢትዮጵያ ዘግቧል።
አቶ ማሙሸት እንዲፈታ ፍርድ ቤት በተደጋጋሚ ውሳኔ ቢሰጥም ፖሊስ ግን አልፈታም ማለቱ ይታወቃል። አቶ ማሙሸት ይህን ዜና እስካጠናከርንበት ጊዜ ድረስ ከእስር አልተፈታም።