አርባ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ኬንያ ውስጥ ተያዙ

ነኅሴ ፳፪ (ሀያ ሁለት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በኬንያ ሜሩ ግዛት ውስጥ በሕገወጥ የገቡ አርባ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞችን መያዙን የአካባቢው ፓሊስ አስታወቀ። ስደተኞቹ በሚዮኖዋ መንደር ውስጥ በሚስጥር ቤት ውስጥ ተደብቀው በአካባቢው ሕዝብ ጥቆማ ትብብር መያዛቸውን ፖሊስ ገልጿል።
ስደተኞቹ ኬንያን አቋርጠው ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመሻገር የመጡ መሆናቸውን በቅርብ ጊዜም ሰማንያ ሕገወጥ ኢትዮጵያዊያን በተመሳሳይ መልኩ መያዛቸውን የጸጥታ ሰራተኞቹ አክለው ገልጸዋል ሲል የኬንያ ቴሊቪዥን ዘግቧል።
ኢትዮጵያ በምጣኔ ሃብት እድገት ማስመዝገቧን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ቀን ከሌት ሲዘግቡ ቢውሉም ኢትዮጵያዊያን ግን ህይወታቸውን ለአደጋ እያጋለጡ ድንበር እያቋረጡ መሰደዳቸውን አላቋረጡም። የአገሪቷ ዕድገት ብዙሃኑን ተጠቃሚ ያላደረገና የገዥው ፓርቲ አባላት ብቻ ከትሩፋቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን ምሁራንና ተቃዋሚዎች በተደጋጋሚ ሲገልጹ ቆይተዋል።