መጋቢት ፳፯ (ሃይ ሰባት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-አቶ መለስ የላኩዋቸው ሽማግሌዎች ቃሊቲ እየተመላለሱ ነው
የአቶ መለስ መንግሥት የወከላቸው ሽማግሌዎች ወደ ማረሚያ ቤት በመሄድ የፖለቲካ እሥረኛ የሆኑ ፍርደኛ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችንና ጋዜጠኞችን ይቅርታ ለማስጠየቅ የማግባባት ሙከራ ማድረግ መጀመራቸውን ለማወቅ ተችሎአል።
የፍትህ ሚኒስቴር ምንጮቻችን እንደገለጹት፤ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተወከሉ ሽማግሌዎች ወደ ማረሚያ ቤት እየተመላለሱ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አብዴፓ) ሊቀመንበርን አቶ ዘሪሁን ገብረእግዚሃብሄርን፣ የአውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ምክትል ዋና አዘጋጅ የነበረውን ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬን፣ የፍትህ ጋዜጣ አምደኛን መምህርት ርዕዮት ዓለሙን እና የቀድሞው የቅንጅት ፓርቲ አባል የነበረችውን ወ/ሮ ሂሩት ክፍሌን በተደጋጋሚ በማነጋገር፤ መንግሥት በይቅርታ ሊፈታቸው እንደተዘጋጀ አስታውቀዋቸዋል፡፡
በዚህ መሠረትም ከርዕዮት ዓለሙ በስተቀር ሁሉም የይቅርታ ፎርሙን ሞልተው ለፍትህ ሚኒሥቴር የይቅርታ ቦርድ መላካቸውን ምንጮቹ ጠቁመዋል።
በይቅርታ ፎርሙ ላይ ለእያንዳንዳቸው ፍርደኞቹ በእውነት ተጸጽተው ስለመፈረማቸው ዋቢ የሚሆኑና ከቤተሰብና ከቅርብ ጓደኛ የተውጣጡ ሦስት ሦስት ሰዎች የድጋፍ ቅጽ መሙላታቸውም ተገልጿል።
ይሁንና ማረሚያ ቤቱ ከወይዘሮ ሂሩት በስተቀር የሌሎቹን የድጋፍ ቅጽ ለፍትህ ሚኒስቴር የይቅርታ ቦርድ ጽ/ቤት ባለማስገባቱ፤ ጉዳያቸው መታየት እንዳልጀመረ እና አንድ ቢሮ ውስጥ ታግቶ እንደሚገኝ ምንጮቹ ገልጸዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በቃሊቲ ማረሚያ ቤት በእሥር ላይ የምትገኘው ጋዜጠኛና መምህርት እርዮት ዓለሙ በማዕከላዊ እስር ቤት ሆን ተብሎ በቀዝቃዛ ሲሚንቶ ላይ እንድትተኛ በመደረጉ በእግሯቿ ላይ ካጋጠማት የቁርጥማት በሽታ በተጨማሪ በጡቷ ላይም ህመም እየተሰማት መሆኑን ፤ የማረሚያ ቤት ምንጮች ተናግረዋል።
ከሁለት ሣምንት በፊት ጀምሮ ርዕዮት በህመም እየተሰቃየች መሆኑን የገለጹት ምንጮቹ፤ ህክምና ታገኝ ዘንድ ለማረሚያ ቤቱ ያቀረበችው ጥያቄም፦” ሴት አጃቢ ፖሊስ የለም”በሚል ምላሽ ሳይሳካ መቆየቱን ተናግረዋል።
ከትናንት በስቲያ ማክሰኞ መጋቢት 25 ቀን ማረሚያ ቤቱ ፦”ሴት አጃቢ ፖሊስ አግኝቻለሁ” በማለቱ ርዕዮት ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ተወስዳ ምርመራ እንደተደረገላት ምንጮቹ አመልክተዋል።
በዚሁ ምርመራዋ፤ ሀኪሞቹ ከጡቷ ላይ ናሙና ፈሳሽ ለምርመራ መውሰዳቸውን የጠቆሙት ምንጮቹ፤ ውጤቱን ለማወቅ ለመጪው ዓርብ መጋቢት 28 ቀን 2004 ዓ.ም ቀጠሮ ተሰጥቷት ወደ ማረሚያ ቤት መመለሷን ገልጸዋል፡፡
________________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide