አቶ መለስ ሙስሊሙ ማህበረሰብ የሚያቀርበውን የመብት ጥያቄ ውድቅ አደረጉት

ሚያዚያ ፲ (አስር) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በአወልያ የተጀመረው ተቃውሞ በመላ አገሪቱ በሚገኙ መስኪዶች እየተስፋፋ መምጣቱን፣ ይህንን ተከትሎም በአዲስ አበባ እና በክልል አካባቢዎች በርካታ ሙስሊሞች እየታሰሩ በሚገኙበት በአሁኑ ጊዜ ፣ ከሙስሊም ማህበረሰቡ አመራሮች ጋር ለመነጋጋር ቀጠሮ የያዙት አቶ መለስ ፣ ከቀጠሮአቸው በፊት ሙስሊሙን ማህበረሰብ በሽብርተኝነት የሚፈርጅ ንግግር ትናንት ለፓርላማው አቅርበዋል። አቶ መለስ በንግግራቸው በአረቡ አለም ውስጥ የሚገኙ የሰለፊያ እስልምና እምነት ተከታዮች በአገራቸው ማእበል ለማስነሳት የቻሉ ሙስሊሞች በኢትዮጵያም ተመሳሳይ ነውጥ ለማስነሳት ሙከራ ማድረጋቸውን ገልጠዋል። የሰለፊያ እምነት ተከታዮችን የአርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ከሆኑት የማህበረ ቅዱሳን ተከታዮች ጋር ያመሳሰሉት አቶ መለስ፣ በእነዚህ ድርጅቶች ውስጥ የሚገኙ ጥቂት አባላት መንግስታዊ ሀይማኖት እንዲኖር ይፈልጋሉ ብለዋል።

አቶ መለስ መንግስት በሀይማኖት ጉዳይ ጣልቃ እየገባ አህባሽ የተባለው አስተሳሰብ እንዲስፋፋ እያደረገ ነው ለሚለው ክስ ከመጂሊሱ ጋር በመተባባር ህገ መንግስቱን ለማስተማር ጥረት ማድረጉን በማመን፣ ሀይማኖቱን ለማስፋፋት ግን አለመሞከሩን ተናግረዋል።

 አቶ መለስ የሙስሊሞችን እንቅስቃሴ ከጀርባ ሆነው የሚያንቀሳቀሱት በግብር ያኮረፉ ፣ በመሬት ስርአቱ ያልተደሰቱ እና በውድድር ምክንያት ከጨዋታ ውጭ የሆኑ ነጋዴዎች ናቸው ሲሉ አክለዋል።

 የአቶ መለስ ንግግር ሙስሊሙ ከሚያቀርበው ጥያቄ ጋር ያልተዛመደ መሆኑን በሼክ ኮጀሌ መስጊድ የሚገኙት ለኢሳት ተደጋጋሚ አስተያየት የሰጡት ኢማም ገልጠዋል። ንግግራቸው በኢትዮጵያ ሰላም እንዲወርድ ሳይሆን ሙስሊሙ የበለጠ እንዲቆጣ፣ ሙስሊሙና ክርስቲያኑ እንዲጋጭ ሆን ተብሎ የታቀደ ነው ያሉት ኢማሙ፣ ሙስሊሙን ለማስደንገጥ እና ማህበረ ቅዱሳንን እንዲጠራጠር ለማድረግ ድርጅቱን በአክራሪነት ሲፈርጁ፣ ክርስቲያኑ ሙስሊሙን እንዲጠራጠር ለማድረግ ደግሞ ሰለፊያን በምሳሌነት አንስተዋል ብለዋል። ንግግራቸው በሙሉ አንዱ ሌላውን እንዲፈራ እና እንዲጠራጠር፣ ለመብቱ በአንድነት እንዳይቆም እና እንዲከፋፈል ለማድረግ ታቅዶ የቀረበ መሆኑን ኢማሙ ገልጠዋል።

  አቶ መለስን ንግግር እንዴት እንደተመለከቱት የጠየቅናቸው አቶ አብየ ያሲን  ያሲን በበኩላቸው … ክርስቲያኑ ህዝብ እውነታውን ሳይረዳ በሙስሊሙ ላይ ጥርጣሬ ሊያድርበት እንደማይገባ፣ ሙስሊሙም እንዲሁ ክርስቲያኑን በደንብ ሳይረዳ ጥርጣሬ እንዳያድረበት ኢማሙ ገልጠዋል።

 የኢሳት የመረጃ ምንጮች እንደሚሉት ሙስሊሙ ማህበረሰብ የጀመረው ጥያቄ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ፣ የአብዛኛውን ሙስሊም ድጋፍ እያገኘና ለአቶ መለስ አገዛዝ ራስ ምታት እየሆነ ነው። አቶ መለስ እንደጻፉት በሚታመን አንድ ሰነድ ላይ የኢህአዴግ አባላት ሳይቀሩ የሙስሊሙ ተቃውሞ እየገፋ መምጣት አስደንግጧቸዋል።

 ባለፈው አርብ በአንዋር መስጊድ የታየው እንቅስቃሴ መንግስትን ክፉኛ ያስደነገጠ እንደነበር ሲገለጥ፣ ተመሳሳይ ተቃውሞ ለማሰማትም መልእክቶች በፌስ ቡክና በስልክ  እየተላለፉ ነው።

በሌላ ዜና ደግሞ አቶ መለስ የስርአታቸው ህልውና በሙስና የተነሳ አደጋ ውስጥ መውደቁን ገልጠዋል። መንግስት ሙስናን የሚዋጋው አንድ እጁን ታስሮ መሆኑን የገለጡት አቶ መለስ፣ የመንግስት ባለስልጣናት በሙስና ላይ የሚደረገውን ትግል እያኮላሹት መሆኑን እና ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ መግባታቸውን ተናግረዋል።

 አቶ መለስ ሰግተዋል በሚል ርእስ በፌስ ቡክ ላይ አስተያየቱን ያሰፈረው ጋዜጠኛ ፍሬው አበበ ” ትላንት ፓርላማ ተገኝተው በተናገሩበት ወቅት እጅግ ተስፋ በቆረጠ አንደበት
“መንግስት አንድ እጁን ታሰሮ ነው የሚታገለው”አሉን፡፡“መንግስትን ደግሞ ማን ነው ሊያሰር የሚችለው? ይህን ያህል ጉልበትስ እንዴት ሊያገኝ ቻለ?” የሚል ገራገር ጥያቄ ሰንቀን እንዳንቸገርም የአሳሪዎቹን ማንነት በአንደበታቸው ነገሩን፡፡ሰዎቹ በቢሮክራሲው ውስጥ የተሰገሰጉ የመንግስት ሌቦች እና ገና ለገና ነገ ሊቀናን ይችላል ያሉ የሌባ ተስፈኞች ናቸው፡፡አቶ መለስ እንዲህ ዓይነት መረር ያለ ንግግር ሲያሰደምጡን
የመጀመሪያቸው አይደለም፡፡በቅርብም በመንግስት መዋቅር ውስጥ ሌቦች መሰጋሰጋቸውን አስረግጠው ነግረውናል፡፡ብዙዎች ግን ይህን አባባላቸውን ሰምተው “አምበሉ እሳቸው አይደሉም ወይ” ከማለት ጀምረው“ማጽዳት ታዲያ የማን ሥራ ነው?”ሲሉ ጠ/ሚኒስትሩን ሸንቆጥ ያደረጉም ነበሩ፡፡ነገሩ ግን እንደምናስበው
ለሰውየው የቀለለ ሆኖ አልታየም፡፡ ብሎአል

ፍሬው  ” የመንግስትን አንድ እጅ ባሰሩት” ሰዎች ምክንያት አቶ መለስ ሁለት መልክ
ያለው አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል፡፡አንዱ ሙስና እጅግ በከፋ መልኩ መንሰራፋቱ የሥርዓቱ አደጋ መሆኑን የመገንዘባቸው ጉዳይ ነው፡፡ሌላው ችግሩን ለመፍታት በቢሮክራሲው ውስጥ የተሰገሰጉትን ሙሰኞች ማጽዳት ከባድ ዋጋ የሚያስከፍል የመሆኑ ጉዳይ ነው፡፡አቶ መለስን ሥጋት ውስጥ የጣለውም ይኽው ጉዳይ ነው፡፡
ያም ሆነ ይህ ሙስና የስርዓቱ አደጋ ሆኖ ብቅ ብሏል፡፡አቶ መለስም ጉያቸውን ማጽዳት ቢቸግራቸውም የሌቦቹን ቡድን መራገም፣አንዳንዴም ብቅ እያሉ ማስፈራራታቸውን ቀጥለዋል፡፡መጨረሻቸው ምን ይሆን? ” በማለት ጠይቋል።

__________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide