ጥቅምት ፮ (ስድስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ብቸኛው የተቃዋሚ ፓርቲ ተመራጩ የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉ ከአቶ ሐይለማርያም ደሳለኝ አዲስ ነገር አለመጠበቃቸውን ሲናገሩ፣ እውቁ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ደግሞ፣ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር “ከእነስታይላቸው ” አቶ መለስን መስለዋል ብለዋል።
አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከፓርላማ አባላቱ ለተነሱት በርካታ ጥያቄዎች መልሶችን የሰጡት፣ የቀድሞው ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ፎቶ ግራፍ ፊት ለፊታቸው ተሰቅሎ በሚታይበት ሁኔታ ነው።
አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር በመልሶቻቸው ሁሉ ላይ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒሰትር ይህን ብለው ነበር በማለት ደጋግመው ሲናገሩ ተስምቷል።
አቶ ሀይለማርያም ዲሞክራሲያዊ ስርአት በኢትዮጵያ በመገንባቱ ለህዝብ ተጠያቂ የሚሆን ስርአት መፈጠሩን በአንድ በኩል ሲገልጹ፣ ዲሞክራሲ እየጎለበተ የሚሄድ ባህል መሆኑን፣ በአንድ ሳምንት ውስጥ ተበጥብጦ የሚጠጣ አለመሆኑን በመጥቀስ ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ ተገንብቷል በማለት የተናገሩትን ንግግር ማፍረሳቸውን ውይይቱን የተከታተለው ዘጋቢያችን ገልጧል።
አቶ ሐይለማርያም ሀሳብን በነጻነት የመግልጽ መብት እየጎለበተ መምጣቱን ፣ በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞችና የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች የአገርን ሰላም ለመበጥበጥና ለማተራመስ የተሰኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ንግግር ዙሪያ ሀሳባቸውን እንዲሰጡ የጠየቅናቸው ብቸኛው የተቃዋሚ ፓርቲ ተመራጭ የሆኑት የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉ አቶ ሐይለማርያም ከቀድሞው የተለየ አዲስ ነገር ይናገራሉ ብለው ጠብቀው እንዳልነበር ገልጠዋል። ለዚህም የሰጡት ምክንያት አቶ ሀይለማርያም ስልጣናቸውን ገና አላጠናከሩም የሚል ነው። 16-10-2012 ግርማ
እውቁ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋችና ምሁር የሆኑት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም በበኩላቸው የአቶ ሐይለማርያም አቀራረብ ከበፊቱ የተለየ አለመሆኑን ገልጠዋል። ፕሮፌሰር መስፍን
ለአቶ መለስ ሲያደርጉ እንደነበረው ታዋቂ ባለስልጣናት በፓርላው ውስጥ አለመገኘታቸው አሳሳቢ መሆኑን ፕሮፌሰር መስፍን ተናግረው አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጊዜ ሊሰጣቸው እንደሚገባም መክረዋል
አቶ ሐይለማርያም አቶ መለስን ደጋግመው መጥቀሳቸውና በአነጋገራቸውም እርሳቸውን ለመምሰል መጣራቸው ሌሎች የኢህአዴግ አባላትን ወደ እርሳቸው ዙሪያ እንዲመጡ ያስችላቸዋል ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ “በዛሬው ንግግራቸው ይህንን ድጋፍ ለማግኘት ያስችላቸዋል ብየ አስባለሁ” በማለት አቶ ግርማ መልሰዋል።
የተከበሩ አቶ ግርማ ፓርላማው ድጋሜ መጠየቅን ቢፈቅድ ኖሮ ሊያሱዋቸው የሚችሉ በርካታ ጥያቄዎች እንደነበሩዋቸው ገልጠዋል
በመጨረሻም ከዛሬው የአቶ ሀይለማርያም ንግግር ተነስተን በኢትዮጵያ ውስጥ አዲስ ለውጥ ይመጣል ብለን ተስፋ ማድረግ እንችላለን በማለት ለፕ/ር መስፍን ወልደማርያም ጥያቄ ያቀረብን ሲሆን፣ ፕሮፌሰሩም ጊዜው ገና ነው በማለት መልሰዋል
በዛሬው የፓርላማ ስብሰባ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒሰትር አቶ መለስ ዜናዊ ባለቤት ወ/ሮ አዜብ መስፍን፣ ሌላው ነባር የህወሀት ታጋይ አቶ አባይ ጸሀየና ሌሎችም ከፍተኛ ባለስልጣኖች አልተገኙም።