አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ በክብር ወደ ሀገሩ እንዲመለስ በመንግስት ጥሪ ቀረበለት።

አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ በክብር ወደ ሀገሩ እንዲመለስ በመንግስት ጥሪ ቀረበለት።
( ኢሳት ዜና ነሐሴ 07 ቀን 2010 ዓ/ም ) የሪዮ ኦሎምፒክ የብር ሜዳሊያ አሸናፊ አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ በስደት ከሚገኝበት የአሜሪካ ግዝት አሪዞና ከነ ቤተሰቡ ወደ ሀገሩ በክብር እንዲመለስ ጥሪ ያደረጉለት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እና ኦሎምፒክ ኮሚቴ ናቸው።
አትሌት ፈይሳ ወደ ሀገሩ በሚመለስበት ጊዜ ከፍ ያለ መንግስታዊ የክብር አቀባበል እንደሚጠብቀው ተገልጿል።
አትሌት ፈይሳ በብራዚል ሪዮ ኦሎምፒክ ሀገሩን ወክሎ በማራቶን በተሳተፈበት ሩጫ የውድድሩን የመጨረሻ ገመድ ሲበጥስ ሁለት እጆቹን ወደ ላይ በማጣመር የህወሓት -ኢህአዴግ አገዛዝ በወገኖቹ ላይ እየፈጸመ ያለውን ግድያና አፈና ለዓለማቀፉ ማህበረሰብ ማጋለጡ ይታወቃል።
የፈጸመውን ድርጊት ተከትሎ በአሜሪካ የጥገኝነት ጥያቄ ያገኘውና ከወራት በኋላ እዚያው በስደት ከቤተሰቦቹ ጋር የተገናኘው አትሌት ፈይሳ፣ ቀደም ባለው ጊዜ ከአቶ ኃይለማርያም መንግስት- ወደ ሀገር ቤት ቢመለስ ችግር እንደማይገጥመው የቃል ዋስትና ቢሰጠውም ሳይቀበለው ቀርቷል።
አትሌቱ በዛሬው ዕለት ከአትሌቲክስ ፌዴሬሽንና ከኦሎምፒክ ኮሚቴ የቀረበለትን ጥሪ በመቀበል ከቤተሰቡ ጋር ወደ ኢትዮጵያ እንደሚገባ የሚጠብውቅ ሲሆን፣ በመንግስት በኩል የጀግና አቀባበል እንደሚደረግለት ታውቋል።