ጥር ፴ (ሠላሳ) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በስዊድን-ስቶኮሆልም በተካሄደው የቤት ውስጥ የ 3 ሺ ሜትር ውድድር አትሊት ገንዘቤ ዲባባ በአስደናቂ ብቃት በማሸነፍ አዲስ የዓለም ክብረወሰን አስመዘገበች።
ገንዘቤ ዲባባ ርቀቱን በ8:ደቂቃ 16 ሴኮንድ 60 ማይክሮ ሴኮንድ በማጠናቀቅ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2007 ዓመተ ምህረት፣ ማለትም ከ 7 ዓመት በፊት በአገሯ ልጅ በአትሌት መሰረት ደፋር ተይዞ የነበረውን ሪከርድ ከ7 ሰከንድ በላይ አሻሽላለች።
ይህ ሰዓት ከ1993 ዓመተ ምህረት ወዲህ በቤትም ሆነ ከቤት ውጪ በተደረጉ የ 3000 ሜትር ውድድሮች በጣም ፈጣኑ ሰዓት ሆኖ ተመዝግቧል።
ገንዘቤ ከ አምስት ቀን በፊት በተካሄደ የቤት ውስጥ የ 1500 ሜትር ውድድር በተመሳሳይ መልኩ አዲስ የዓለም ክብረ ወሰን ጨብጣለች።