አቡነ ዘካርያስ የተጭበረበሩትን 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ራሳቸው ከፈሉ።

ግንቦት ፪ ( ሁለት ) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ቀደም ሲል የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት አስተዳደር የነበሩትና አሁን የኒውዮርክና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የሆኑት አቡነ ዘካርያስ፣ በሐሰተኛ ሰነድ ተጭበርብረው ሕንፃበመግዛታቸው የከሰረውን ገንዘብ ከምዕመናን በማሰባሰብ ራሳቸው ፈጸሙ፡፡
የቅዱስ ሲኖዶስ አባል የሆኑት አቡነ ዘካርያስ ቀደም ሲል ያስተዳድሩት በነበረ ሀገረ ስብከት ሥር ለሚገኙ ደቀ መዛሙርት ማሠልጠኛና ለአብነት ትምህርት ቤቶች ድጋፍ እንዲሆን በማሰብ ነበር አንድ ሕንፃ ለመግዛት ተስማምተው ከ1.6 ሚሊዮን ብር በላይ ቀብድ የከፈሉት።
ይሁንና ሕንፃውን ሊሸጥላቸው የተስማማቸው ግለሰብ ውሉን እንዲፈጸም ያስፈጸማቸው በሐሰተኛ የሰነድ ማስረጃ በመሆኑ ገንዘቡን እንደተቀበለ ወዲያውኑ ተሰውሯል። ሻጭ መሰወሩ እንደታወቀ የሰበካ ጉባዔው የሥራ አስፈጻሚ አባላት በሕግ ሲጠየቁ ‹‹መንፈሳዊ አባታችን ስላዘዙን ገንዘቡን ወጪ አድርገናል›› በማለት የሰጡትን ቃል ተከትሎ አቡነ ዘካርያስ‹‹ኃላፊነቱን እኔ እወስዳለሁ፤›› በማለታቸው፣ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት በነፃ ተሰናብተዋል፡፡
አቡኑ ይህን ተከትሎ ከምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ተነስተው ወደ አሜሪካ የተመደቡ ቢሆንም፣ ላለፉት ስምንት ዓመታት ሳይከፍሉ የቆዩትንና ኃላፊነት የወሰዱበትን 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በሁለት የዕለተ ሰንበት የምዕመናን ተሳትፎ በማሰባሰብ ሰሞኑን ገቢ ማድረጋቸውን የሪፖርተር ዘገባ ያመለክታል።