ኀዳር ፳፫ (ሃያ ሦስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-“በአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ሰበብ በከተማዋ ዙርያ ያሉ ወገኖቻችንን ማፈናቀል በመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የተፈፀመ ጥቃት ነው” ያለው አርበኞች ግንቦት7፣ በማስተር ፕላኑ ሰበብ የሚፈናቀሉ ገበሬዎች የሁላችን ወላጆች፣ ወንድሞችና እህቶች በመሆናቸው ይህንን ድርጊት በመቃወም ላይ ያሉት የኦሮሞ ተወላጅ ወገኖቻችን ትግል ፍትሀዊ በመሆኑ ንቅናቄው ከጎናቸው ይቆማል።” ብሎአል።
በጎንደር ህወሓት ከሶስት ሺህ በላይ ዜጎቻችንን ያጎረበት እስር ቤት በእሳት ሲጋይ ዜጎች ተቆልፎባቸው እንዲነዱ መደረጉን ያወሳው ንቅናቄው፣ ከእሳቱ በእድል ያመለጡት በጥይት መገደላቸውን፣ ኢትዮጵያዊያን እንዲህ ዓይነቱን ጭካኔ የሚያውቁት በፋሺስት ጣሊያን ወረራ ጊዜ መሆኑንና ይህን ጥቃት በመቃወም ላይ ያሉ የአማራ ተወላጅ ወገኖቻችን ትግል ፍትሀዊ በመሆኑ አርበኞች ግንቦት 7:የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ ከጎናቸው እንደሚቆም ገልጿል።
“የህወሓት አገዛዝ የትውልድ ቦታ፣ ቋንቋና ዘር ሳይለይ በኢትዮጵያዊያን ሁሉ ላይ የተደቀነ አደጋ መሆኑ ከምንጊዜውም በላይ ዛሬ ግልጽ ሆኗል” የሚለው ንቅናቄው፣ “የሁላችን የጋራ ጠላት የሆነው ህወሓት መኖሩ በዘውግ የተከፋፈለውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ወደ አንድነት የሚያመጣ ታላቅ ኃይል በመሆኑ፣ ይህ የመከራና የመጠቃት ወቅት የምንቀራረብበት ወቅት ሊሆን ይገባል።” ሲል አክሏል።
ለቀምት፣ ሀረር፣ ሱልልታ እና ሌሎች በርካታ የኦሮሚያ ከተሞች ውስጥ ለደረሱ ጥቃቶች ባህር ዳር፣ ጎንደር፣ ደሴ፣ ሀዋሳ፣ መቀሌ፣ አሶሳ፣ ሁመራ፣ ጋምቤላ ውስጥ ተቃውሞ መሰማት አለበት የሚለውን ንቅናቄው፣ በጎንደርና ባህርዳር ለደረሰውም ጥቃት አዳማ፣ ጅማ፣ ሆሳዕና፣ ጅግጅጋ፣ አክሱም ላይ ተቃውሞ መሰማት መጀመር አለበት ብሎአል።በማንኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ለሚደርሰው በደል መላዋን ኢትዮጵያ ሊያሳምም እንደሚገባ፣ መከፋፈላችን መከራችን ማብዛቱንና የህወሓት እድሜን ማራዘሙን በመግለጽ፣ ይብቃ ብሎአል።