በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ላይ የቀረበውን ይግባኝ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውድቅ አደረገው

ኀዳር ፳፫ (ሃያ ሦስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ በእነ ዘመነ ካሴ መዝገብ ከ2 ኛ እስከ 5 ኛ ድረስ ለተጠቀሱት ተከሳሾች የመከላከያ ምስክር ሆነው እንዲቀርቡ ተጠይቆ እስር ቤቱ በተደጋጋሚ ጊዜያት ሳያቀርባቸው ቢቆይም፣ ተከሳሾቹ ለጠ/ፍርድ ቤት ባመለከቱት መሰረት፣ የፌደራል አቃቤ ህግ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ምስክር ሆነው እንዳይቀርቡ ያቀረበውን ይግባኝ ህዳር 23 ቀን 2008 ዓ.ም. በዋለው ችሎት ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ይግባኙን ውድቅ አድርጎታል፡፡
የፌደራል አቃቤ ህግ አቶ አንዳርጋቸው በእነ ጀኔራል ተፈራ ማሞ መዝገብ እና በእነ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ መዝገብ ላይ ክስ ቀርቦባቸው በእድሜ ልክና በሞት እንዲቀጡ ተወስኖባቸው የህዝባዊ መብታቸው የተሻረ በመሆኑ በምስክርነት ሊቀርቡ እንደማይችሉ መቃወሚያ አቅርቧል።
የልደታ ፍርድ ቤት በበኩሉ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ምስክርነት እንዲሰጡ ከወሰነ በኋላ የቃሊቲ ማረሚያ ቤት ‹‹ትዕዛዝ አልደረሰኝም የተፃፈው ለቃሊቲ ሳይሆን ለአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት የሚል ነው›› እና ሌሎችም ምክንያቶች በመደርደር በተደጋጋሚ አቶ አንዳርጋቸውን ሳያቀርብ ቢቆይም፣ ተከሳሾቹ አቶ አንዳርጋቸው እንዲቀርቡላቸው የጠየቁት ለዋስ አሊያም ልዩ አዋቂ ምስክር ሆነው ሳይሆን ነበሩበት የተባለውን ጉዳይ ለመናገር በመሆኑ ለምስክርነት ሊቀርቡ ይገባል በሚል የፌደራል አቃቤ ህግ ያቀረበውን ተቃውሞ ፍርድ ቤቱ ውድቅ አድርጎታል።
በተጨማሪ በእነ ዘላለም ወርቃገኘሁ የክስ መዝገብ ከተከሰሱት መካከል 1ኛ ተከሳሽ አቶ ዘላለም ወርቃገኘሁም አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን በመከላከያ ምስክርነት ጠርቷቸዋል፡፡ በሌሎች የክስ መዝገቦች ከአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ጋር ተገናኝታችኋል የተባሉ ተከሳሾችም የመከላከያ ምስክር አድርገው ሊጠሯቸው እንደሚችሉ የነገረ ኢትዮጵያ ዘግቧል።