መጋቢት ፱ (ዘጠኝ) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የመንግስት ኮሚዩኒኬሺን ጽ/ቤት ከህዝብ ባሰባሰበው መረጃ እና ከክልሎች የተላከው የጽሁፍ ሰነድ እንዳመለከተው ፤ የኦሮምያ ፤ የአማራ እና የደቡብ ክልል አርሶ አደሮች ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር ወስዳችሁ ግብር እና የማዳበሪያና የምርጥ ዘር እዳችሁን አንክፍልም ብላችኃል በሚል እየታሰሩና ስቃይ እየደረሰባቸው መሆኑ ተመልክቷል።
“በእድሜ የገፉ እናት አባቶችን ታስረው ይንገላታሉ ፤ ከብቻችንን ከቤታችን በሃይል ነድተው ያስራሉ ፤ በሬ ከቀንበሩ ፈተው ይወስዳሉ፣ የታጠቁ የመንግስት የፀጥታ አሰተዳደር እና ሚልሻዎች በአርሶ አደሩ ላይ ድብዳ ይፈጽማሉ” ሲሉ አርሶደሮች ተናግረዋል፡፡
በጎጃም አካባቢ የመንግስት ታጠቂዎች ክፍያውን እናስከፍላለን በሚል ከእርሻ ላይ በሬ ለመፍታት ባደረጉት ሙከራና፣ በሬዎቼን ከቀንበር ላይ አላስፈታም ባለ አርሶ አደር መካከል በተፈጠረ ውዝግብ፤ የአምስት ሰዎች ህይዎት ጠፍቷል፡፡ በግጭቱ የሞቱት አርሶ አደር በሪሁን ፈንታ፣ ባለቤቱና የመጀመሪያ ልጁ ሲሆኑ፣ ሁለት ደግሞ የመንግስት ታጣቂዎች ናቸው።
የመንግስት ከሚዩኒኬሺን ጽ/ቤት መረጃ እንደሚያሳየው ባለፈው ዓመት በነበረው የአካባቢ ምርጫ ፣ ህዝቡ ከምርጫ ውጭ እንዳይሆን በማሰብ የማዳበሪያ እና የግብር እዳ ሳይጠየቅ ከርሟል።
በኦሮምያ ላሞቻቸውን በእዳ አስረክበው 13 ወጣቶች መሰደዳቸውን፣በአማራ ክልል 57 ወጣቶች መሸፈታቸውን፤ በደቡብ 31 አርሶ አደሮች እርሻ አቁመው ሎሌነት መቀጠራቸው በጥናቱ ተመልክቷል።
በዚህ ሁኔታ ከቀጠለ ገዢው ፓርቲ ከአርሶ አደሩ የሚያገኘው ድምጽ አይኖርም ብሎአል ሪፖርቱ። ኢህአዴግ አርሶ አደሩን ግብር ለማስከፈል አዲስ እንቅስቃሴ ለመጀመር ቢያስብም፣ መጪውን ምርጫ በመፍራት ለጊዜው ለመተው እንደወሰነ መረጃዎች ያመለክታሉ።