ታህሳስ 14 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩትና በአሁኑ ወቅት የህግ ስርአት ምርምር ተቋም ዳይሬክተር የሆኑት አቶ መንበረጸሀይ ታደሰ መቀሌ ተደርጎ በነበረው የሰብአዊ መብቶች ቀን በአል ላይ ባቀረቡት ጽሁፍ “ኢትዮጵያ ውስጥ ፍትህ የሚባል ነገር ጠፍቷል፤ ገንዘብ ያለው ሰው እውነት ባይኖረውም፣ እውነት የያዘውን ሰው እያሸነፈው” ሲሉ ገለጡ
የመንግስት ባለስልጣናትን ሳይቀር ያስደነገጠ ንግግር ያቀረቡት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የአንድ ወቅት የህግ አማካሪ የነበሩት አቶ መንበረ ” ህጋችን ሁሉ በኩረጃ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ፣ ኢትዮጵያዊ ሽታ አጥቷል” ሲሉ በመናገር በቅርቡ ከውጭ አገር ኮርጀን የደነገገው ነው እያሉ አቶ ሽመልስ ከማልና አቶ መለስ ዜናዊ በአደባባይ ስለሚናገሩለት የጸረ ሽብርተኝነትና የፕሬስ ህግ ትችት ማቅረባቸውን ዘጋቢያችን ገልጧል።
የኢትዮጵያ ባለስልጣናት በፍትህ እጦት ዙሪያ ተችዎች ሊሚያቀርቡት ትችት ዘወትር የሚሰጡት ምልስ ” ህጉ ከውጭ አገር የተኮረጀ ነው የሚል መሆኑን ” ያስታወሰው ዘጋቢያችን፣ ለ17 አመታት የኢትዮጵያን የፍትህ መዋቅር ማሻሻያ የመሩትና ለመለስ መንግስት የህግ ምክር ሲሰጡ የቆዩት አቶ መንበረ ” በትውስት ህግ በማውጣት የሚቀድመን ሌላ አገር ያለ አይመስለኝም፤ ነገር ግን ዳኞቻችን እንኳ ህጋችንን በትክክል ለመረዳት በማይችሉበት ደረጃ በመድረሳቸው፣ ህብረተሰቡ በየጊዜው ምሬቱን እየገለጠ ነው። ይህም ምሬት ተገቢ በመሆኑ የፍትህ ስርአቱ ከስር መሰረቱ መለወጥ አለበት ” ሲሉ አክለዋል።
ህብረተሰቡ እውነት የሚለውና ዳኞች እውነት የሚሉት ነገር አልጣጣም ማለቱን ያወሱት አቶ መንበረ፣ ” የገንዘብ አቅም ያለው ሰው ይረታል፣ አቅም የሌለው እውነትን ቢይዝ እንኳ ማሸነፍ አይችልም። ተበዳይና በዳይን ለማለየት በማይቻልበት ደረጃ ተደርሷል። አራት ኪሎ የሚወጣና የሚጸድቅ ህግ መርካቶን እንኳ ለማስተዳደር የማይችል ሆኖ ተገኝቷል” ሲሉ ደምድመዋል።
የአቶ መንበረጸሀይ ያልተለመደ ንግግር የመለስ መንግስት የህግ የበላይነት እንዳለ፣ የፍትህ ስርአቱ መሻሻሉን ሲገልጥ የነበረውን ሙሉ በሙሉ ገደል የከተተ ሆኖ ተወስዷል።
የፍትህ ስርአት መዋቅሩን ላለፉት 17 አመታት የመሩት አቶ መንበረ፣ ከዚህን አመት በሁዋላ በድንገት ብድግ ብለው ፣ ፍትህ ጠፍቷል ማለታቸው ግለሰቡን ከመንግስት ጋር ሳያጋጫቸው እንደማይቀር ዘጋቢያችን ጠቁሟል።
የህወሀት ቀንደኛ ደጋፊ የሆኑት አቶ መንበረ በርካታ ዳኞች የገዢው ፓርቲ ተቀጥላ እንዲሆኑ ከፍተኛ ግፊት ሲያደርጉ እንደነበር ስራቸውን የለቀቁ ዳኞች በተደጋጋሚ የሚናገሩት እውነታ ነው።
አቶ መንበረ ከአመት በፊት ስራቸውን የግል ችግር አለብኝ የሚል ምክንያት አቅርበው መልቀቃቸው ይታወቃል።
በሌላ በኩል ደግሞ ላለፉት 10 አመታት ህዝቡ የመንግስትን አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል ጥረት ቢደረግም ለውጥ ለማምጣት አለመቻሉን የሲቪል ሰርቨስ ሚኒስትር የሆኑት አቶ ጁነዲን ገለጠዋል።
አቶ ጁነዲን ይህን የገለጡት የሲቪል ሰርቪስ ተወካዮችን ሰብስበው ባነጋገሩበት ወቅት ነው።አቶ ጁነዲን ” ህዝቡ ስለማይናገር፣ ስለማይቆጣና ስለሚፈራ መብቱን ማስከበር” አለመቻሉን ተናግረዋል።
ህገመንግስቱ መብት ተከብሯል ቢልም፤ ህዝቡ ግን ባለስልጣናትን ስለሚፈራና ስለማይቆጣ መብቱን ማስከበር አለመቻሉን አቶ ጁነዲን ተናግረዋል።አቶ ጁነዲን ህዝቡ ለምን እንደማይቆጣና ለምን እንደሚፈራ ምክንያቱን አላስቀመጡም።