ፍርድ ቤት በእነ ኤልያስ ክፍሌ የክስ መዝገብ በሽብርተኝነት ወንጀል በተከሰሱት የመከላከያ ምሥክሮችን ትላንት አደመጠ

13 ቀን 2004 /

ኢሳት ዜና:-የፌዴራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሦስተኛ ወንጀል ችሎት በእነ ኤልያስ ክፍሌ የክስ መዝገብ በሽብርተኝነት ወንጀል በተከሰሱት የፖለቲካ ፓርቲ የአመራር አባል አቶ ዘሪሁን ገብረእግዚሃብሄር፣ የአውራምባ ታይምስ ምክትል ዋና አዘጋጅ ውብሸት ታዬ፣ ጋዜጠኛ ርዮት ዓለሙ እና ሂሩት ክፍሌ ላይ የመከላከያ ምሥክሮችን ትላንት አደመጠ፡፡

አርቲስት ደበበ እሸቱ የርእዮት ዓለሙ የመጀመሪያ ተከላካይ ምሥክር ሆኖ ርዮትን ከኢትየጵያን ሪቪዩ ድረ ገጽ ጋር እንዴት እንዳገናኛቸው ለፍርድ ቤቱ ትላንት አስረድቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ ለጋዜጠኛ ርእዮት ዓለሙ የሙያ ምሥክርነት ሊሰጡ የመጡትን የመድረክ አመራር አባልና የኦሮሞ ህዝቦች ኮንግረንስ /ኦህኮ/ ፓርቲ ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና እና   የሕግ ባለሙያ የሆኑትን ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለማርያምን “በሕግ ላይ ሙያዊ ምስክር አይሰጥም ሕግ የመተርጎሙ ሥራ የኔ ብቻ ነው” በማለት አልቀበልም ብሎ መልሷቸዋል፡፡ ሁለቱ ምሁራን የፍርድ ቤቱን ስንብት በዝምታ ተቀብለው ሲወጡ “የቀኝ ዳኛው ችሎቱን መከታተል ከፈለጋችሁ መቀመጥ ትችላላችሁ” ሲሏቸው ዘወር ብለው በትዝብት አይን አይተዋቸው ወጥተዋል፡፡

ተከሳሾች ክሳቸውን በቃላቸው ያስተባበሉ ሲሆን ጋዜጠኛ ርዮት ዓለሙ በሰጠችው ቃል “እኔ በሙያዬ ጋዜጠኛ ነኝ፣ ይህን የሚያውቀው አርቲስት ደበበ እሸቱ  የኢትዮጵያን ሪቪዩ ድረ ገጽ ባለቤት ጋዜጠኛ ኤልያስ ክፍሌ ሪፖርተር ሲፈልግ እኔን አገናኘው፣ እኔም ፈቃደኛ ሆንኩኝ፡፡ በዚህም ለ2 ወር ከምናምን የተለያዩ ዜናዎችን ሰርቻለሁ፡፡ መጋቢት መጨረሻ 2003 አካባቢ በቃ የሚል በየአካባቢው እንደተፃፈ ኤልያስ መረጃ እንዳለውና ፎቶ አንስቼ እንድልክለት ጠይቆኝ ልኬለታለሁ፡፡” ብላለች።

ርእዮት አክላም “ሌላው ፍርድ ቤቱ እንዲያውቀው የምፈልገው በርካታ መርማሪዎችና ትልልቅ ኃላፊነት ያላቸው ሰዎች፣  በፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ምክትል ኮሚሽነር የሆኑት ሀሰን ሺፋ-ን ጨምሮ፣  በሌሎች ተከሳሾች ላይ በሀሰት መስክረሽ ነፃ ውጪ ብለውኛል፡፡ ይህን አልቀበልም በማለቴ እርሳቸው እንዲህ ዓይነት አቋም ካለሽ ለምን ጫካ አትገቢም ብለውኛል” በማለት ተናግራለች፡፡

ርእዮት “አንድ ዐቃቤ- ሕግ ፣ እዚህ አሁን የሌለ፣ በሀሰት እንድመሰክር አባብሎኝ አልቀበል በማለቴ ከ25 ዓመት እስከ እድሜ ልክ እሥራት ይጠብቅሻል ብሎኛል፡፡ ይህን ሁሉ እንቢ በማለቴ በማዕከላዊ እሥር ቤት ለ13 ቀናት በጨለማ ክፍል ብቻዬን አሥረውኛል፡፡ ከዚህ ስወጣም አንዱ መርማሪ እያሳሳቀኝ አንዷ ተደብቃ በቪዲዮ ልትቀርጸኝ ሞክራ ፊቴን ከልዬ ራሴን ተከላክያለሁ፡፡ እኔ ጋዜጠኛ ነኝ በሰላማዊ መንገድ መንግሥትን እቃወማለው፡፡ ኢሜሌ ላይ በርካታ ስህተት ተሰርቶብኛል፡፡ በኢሜሌ ላይ የነ ጆሃር ሙሀመድን ጽሑፍ ከተውብኝ ተጠያቂ ሊያደርጉኝ ይፈልጋሉ፡፡ የትርጉም ድርጅቱ ሁሉ ከእነርሱ ጋር ግንኙነት እንዳለው በሚያስመስል መልኩ ሽብር ሽብር የሚል ትሩጉም ነው ያቀረቡት፡፡ ለምሳሌ፣ አንድ ቦታ ላይ አመጽ ትክክለኛ አማራጭ ነው ብለው አቅርበዋል፡፡ ይህ ተቃዋሚ ስለሆንኩ ብቻ የተሰራብኝ ደባ ነው፡፡” ብላለች።

 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢብዴፓ) ሊቀመንበር አቶ ዘሪሁን ገብረእግዚያብሄር በበኩላቸው “እኔ የፖለቲካ ፓርቲ ሊቀመንበር ነኝ፣ሽብርተኝነትን እናወግዛለን መቼም ቢሆን ሽብርተኝነትን ደግፈን አናውቅም፣አንደግፍም፤ ከጋዜጠኛ ኤልያስ ክፍሌ ጋር ያለን ግንኙነት የፖለቲከኛና የጋዜጠኛ ነው፡፡ ከእርሱ የተቀበልኩት ገንዘብም ተልዕኮም የለም፡፡ ነገር ግን ለፓርቲ የሚገባ ገንዘብ ከአንድ ግለሰብ ተቀብያለሁ፣ ይህ ደግሞ በፓርቲው ሰነድ ውስጥ ይገኛል፡፡” ብለዋል።

“ፓርቲያችን ግንቦት 20 ቀን 2003 ዓ.ም ሠላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ጥያቄ አስገብቶ ማስፈራሪያና ዛቻ ከመንግሥት ሲደርስብን ነበር፤ ፓርቲያችን የተቋቋመው መንግሥትን ለመቃወም ነው፣ በሕጉ መሠረት ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ በ24 ሰዓት ውስጥ ማሳወቅ አለበት እንጂ ማስፈቀድ አለበት አይልም፣ መለስ በቃህ የሚለው መፈክርም በፓርቲያችን የተፃፈ ነው፡፡ ደህንነቶች ግማሾቻችንን ደብድበውናል፣ እኔ ጸጉሬ እየተነጨ ነው የተደበደብኩት” በማለት ለፍርድ ቤቱ አሳውቋል፡፡

በኤልያስ ክፍሌ የክስ ፋይል ሦስተኛ ተከሳሽ ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ ዐቃቤ- ሕግ ባቀረበብኝ የስልክ፣ የኢሜል ልውውጥ ክሶች ላይ ነው የማስተባብለው አለ ካለ በሁዋላ ” እኔ መብቴን በተጠቀምኩና ሙያዬን በመተግበሬ ነው የተከሰስኩት፣ የሕገ መንግሥት አንቀጽ 29 ንዑስ አንቀጽ 2/4 ይሄን ይፈቅድልኛል፣ ተሸሽሎ የወጣው የፕሬስ አዋጅ አንቀጽ 7 ይህን ማድረግ እንደምችል ያስቀምጣል ይሄ ይያዝልኝ” ካለ በሁዋላ ፤ “በኢሜል ልውውጡ የተጨመሩ ቃላት ወደ አማርኛ ሲተረጎም የተዛቡ ቃላት ተጨምረውብኛል፣ ይሄም ፍርድ ቤቱን ለማጭበርበር ነው፤ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሻለሁ የሚል አለ፣ ሰኔ 23 ቀን 2003 ዓ.ም ኢሜል እንደተፃፃፍኩ የቀረበ አለ፣ ነገር ግን እኔ ሰኔ12 ቀን በቁጥጥር ሥር ውዬ ሰኔ 13 ቀን ፍርድ ቤት ቀርቤያለሁ፣ እንግዲህ ከታሰርኩ ሳምንት ሆኖኝ ሁሉ ተፃፅፊያለሁ ማለት ነው፡፡ እኔ ጋዜጠኛ ነኝ ነገር ግን የጦር ጄኔራል አድርገው አቅርበውኛል፡፡ ጦርነት እየተካሄደነው የሚል አለ፡፡ ውጪ አገር ላለ ወንድሜ በእንግሊዝኛ አዛውንት አባቴ ታሞ ኦፕሬሽን ላይ ነው ይታከም ያልኩትን የጦርነት ኦፕሬሽን ነው ብለው ተርጉመውታል፡፡” ሲል ተናግሯል።

“ገንዘብን  በተመለከተም እኔ ወንድሜም ሆኑ ጓደኞቼ ውጭ አገር አሉ፣ ብር ሲልኩልኝ በሕጋዊ ባንኮች ነው የምቀበለው ያውም ፓስፖርቴን ፎቶ ኮፒ እያደረኩ፡፡ ጋዜጠኛ ኤልያስ ክፍሌ አንድ ጊዜ መቶ ዶላር ሌላ ጊዜ ደግሞ ሁለት መቶ ዶላር ልኮልኛል” ብሎአል።

ፍርድ ቤቱ የመጨረሻውን ምሥክር ለማድመጥና የማጠቃለያ ክርክር ለመስማት ለዛሬ ዓርብ ታህሳስ 13 ቀን 2004 ዓ.ም ጊዜ ቀጠሮ ሰጥቶ ችሎቱ ተበትኗል፡፡