አምነስቲ ኢንተርናሽናል በኢትዮጵያ ውስጥ በጸረ ሽብርተኝነት ሰበብ የሚካሄደው እስር የፖለቲካ ተቃውሞን ለማፈን ተብሎ የተደረገ ነው አለ

06 ቀን 2004 /

ኢሳት ዜና:-አምነስቲ ባወጣው ሪፖርት እንዳመለከተው በኢትዮጵያ ውስጥ ካለፈው መጋቢት ወር ጀምሮ 108 የተቃዋሚ አባላትና 8 ጋዜጠኞች ታስረዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት፣  ተቃዋሚዎችንና ተችዎችን በጸረ ሽብር ትግል ስም ዘብጥያ እያወረደ ነው ሲል የሰብአዊ መብት ተቋሙ በሪፖርቱ አመልክቷል።

አብዛኞቹ  አሸባሪ ተብለው የታሰሩት በሙሉ መንግስትን በመተቸት የሚታወቁ ናቸው የሚለው አምነስቲ፣ የታሰሩበት ምክንያትም መንግስት የፖለቲካ ለውጥ እንዲያካሂድ ያሳሰቡ፣ ሰላማዊ ሰልፍ እንዲፈቀድላቸው የጠየቁና የምርመራ ጋዜጠኝነት ለማካሄድ ሲሰሩ የነበሩ ናቸው ።

መንግስት በእስረኞች ላይ ያቀረበው ማስረጃ ግለሰቦቹን በሽብርተኝነት ሊያስከስሳቸው እንደማይችል የሚገልጠው አምነስቲ፣ እስረኞች  ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብታቸውን ተጠቅመው ሀሳባቸውን መግለጻቸው ሀጢያት አለመሆኑን ጠቁሟል።

ሰላማዊ ሰልፍ መጥራት ሁሉ በኢትዮጵያ በሽብርተኝነት ወንጀል እንደሚያስከስስ አምነስቲ አትቷል። ፍርድ ቤቱ ራሱ የገዢው ፓርቲ የፖለቲካ አጀንዳ ማስፈጸሚያ መሆኑን የሚገልጠው አምነስቲ ፣ ጠቅላይ ሚኒሰትር መለስ ዜናዊ እስረኞቹን በአደባባይ ወንጀለኛ ብለው መፈረጃቸው ሂደቱ በሙሉ ፖለቲካዊ ይዘት እንዳለው ያመለክታል።

አቶ መለስ እስረኞችን ወንጀለኞች በማለት ከፍርድ በፊት ውሳኔ መስጠታቸው በዳኞች ላይ ጫና እንደሚፈጥርና እስረኞችም ከፍርድ ቤት ውሳኔ በፊት ነጻ ተደርገው የመቆጠር መብታቸውን እንደሚጋፋ ጠቅሷል።

አብዛኞቹ እስረኞች በማእከላዊ እስር ቤት ውስጥ ቶርቸር ወይም ሰቆቃ እንደተፈጸመባቸውና ሳይወዱ በግድ ራሳቸውን የሚወነጅል ወረቀት እንዲፈርሙ መደረጋቸውን ገልጧል።

አምነስቲ አሁን በሚታየው ሁኔታ እስረኞቹ ፍትሀዊ የሆነ የፍርድ ውሳኔ ያገኛሉ ተብሎ እንደማይጠበቅ ገልጦ፣ በአዲስ አበባ የሚገኙ የዲፕሎማቲክ አባላት ሂደቱን በቅርበት እንዲከታተሉት ጠይቋል።

አቶ መለስ ዜናዊ የማሰሩ ተግባር እንደሚቀጥል መናገራቸውን ተከትሎ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ በኦሮሚያ ክልል ከ135 በላይ ሰዎች መታሰራቸውን አጋልጧል።

አምነስቲ በተቃዋሚዎች እና ጋዜጠኞች ላይ የሚካሄደው እስር በኢትዮጵያ ውስጥ መንግስትን መቃወም የሚባል ነገር እንዳይኖር ማድረጉን እና እጅግ ጠባብ የሆነውን የፖለቲካ ምህዳር ሙሉ በሙሉ የሚዘጋው መሆኑን አመልክቷል።