ኢሳት (ታህሳስ 21 ፥ 2009)
አሜሪካ 35 የሩሲያ ዲፕሎማቶች እስከፊታችን እሁድ ድረስ ሃገሪቱን ለቀው እንዲወጡ አዘዘች። በአሜሪካ ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ ልዩ ትዕዛዝ የተላለፈውን ይኸው ውሳኔ ሩሲያ ባለፈው ወር በአሜሪካ ተካሄዶ ከነበረው ምርጫ ጋር በተገኛኘ እንደሆነ ታውቋል።
የአሜሪካ ባለስልጣናት ሩሲያ በምርጫው ሂደት ላይ የኢንተርኔት ሻጥር ለመፈጸም ስትንቀሳቀስ እንደነበር በማስረጃ መገኘቱ ይፋ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።
የአሜሪካ ከፍተኛ የደህንነት ሃላፊዎች ሲከታተሉት ነበር የተባለውን ይህንኑ ጉዳይ ተከትሎ ፕሬዚደንት ኦባማ 35ቱ የሩሲያ ዲፕሎማቶች ከነሙሉ ቤተሰቦቻቸው ሃገሪቱን ለቀው እንዲወጡ አዘዋል።
ከዲፕሎማቶቹ መባረር በተጨማሪ በአሜሪካ የሜሪላንድ ግዛትና በኒው ዮርክ ከተማ ከስለላ ጋር የተገናኙ መረጃዎች ሲሰበሰቡ ነበር የተባሉ ሁለት ተቋማት እንዲዘጉ መደረጉንም አሶሼይትድ ፕሬስ ዘግቧል።
ባለፈው ወር በአሜሪካ ተካሄዶ በነበረው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ወቅት የሩሲያ የኢንተርኔት የስለላ ድርጊት ፈጻሚ አካላት በተለይ በዴሞክራቲክ ፓርቲ እና በእጩ ተወዳዳሪዋ ሂላሪ ክሊንተን የምርጫ ዘመቻ ላይ የስለላ ድርጊት እንዲፈፅሙ ሲገለፅ መቆየቱ የሚታወስ ነው።
ይሁንና የሩሲያው ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን ሃገራቸው በምርጫው ሂደት ላይ ጣልቃ እንዳልገባች በማስተባበል ድርጊቱ መሰረተ-ቢስ እንደሆነ ሲገለጹ ቆይተዋል።
በዚሁ ጉዳይ ዙሪያ ምርመራን ያካሄዱ የቴክኖሎጂው ባለሙያዎች በበኩላቸው ጥቃቱ ስለመፈጸሙ በቂ መረጃ መኖሩን በመግለጽ ላይ ናቸው።
ተሰናባቹ የአሜሪካ ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ ሃገራቸው በሂደት ከድርጊቱ ጋር ግንኙነት ባላቸው አካላት ላይ ተመሳሳይ እርምጃን እንደትወስድ አስታውቀዋል። በርካታ የሃገሪቱ የህግ አውጭ አካላት በበኩላቸው አሜሪካ ጠንካራ የአጻፋ ዕርምጃ መውሰድ ይኖርባታል ሲሉ ዕርምጃውን አወድሰዋል።
አሜሪካ የወሰደችውን ይህንኑ ውሳኔ ተከትሎ ሩሲያ የአሜሪካና የምዕራባውያን የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ የሚማሩበትና በሞስኮ ከተማ የሚገኝ አንድ ትምህርት ቤት እንዲዘጋ ወስናለች።
እንዲሁም የአሜሪካ ኤምባሲ ባልደርቦች ለሽርሽር የሚጠቀሙበት አንድ ማዕከልም የኤምባሲው ባልደርቦች እንዳይገለገሉበት እገዳ የተጣለ ሲሆን፣ ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን የአጸፋ ዕርምጃዎችን እንደማይወስዱ አለም አቀፍ ብዙሃን ዘግበዋል። ፕሬዚደንት ፑቲን በራሺያ የሚኖሩ የአሜሪካ ዲፕሎማቶችና ቤተሰቦቻቸው በክሬምሊን የሚገኘውን የገና ዛፍ እንዲጎበኙ ጋብዘዋል።
አሜሪካና ሩሲያ በሶሪያ የተካሄድ ካለው ጦርነት ጋር በተያያዘ አለመግባባት ውስጥ መቆየታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ሃሙስ መውሰድ የጀመሩት ዕርምጃም ሁለቱ ሃገራት ወደ ቀዝቃዛው ጦርነት ይወስዳቸዋል ተብሎ ተገምቷል።
ሩሲያ በፕሬዚደንታዊ ምርጫው ጣልቃ አልገባችም የሚል አቋም ያላቸው ተመራጩ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው በጉዳዩ ዙሪያ በቀጣዩ ሳምንት ከደህንነት ሃላፊዎች ጋር እንደሚመክሩ አስታውቀዋል።