(ኢሳት ዲሲ–ጥር 28/2011)አሜሪካ በኬንያ ናይሮቢ ለሚኖሩና ወደዚያ ለሚጓዙት ዜጎች የጉዞ ማስጠንቀቂያ አወጣች።
ብሪታኒያም ተመሳሳይ የጉዞ ማሳሰቢያ ይፋ ማድረጓ ታውቋል።
ምዕራባውያንን ኢላማ ያደረገ የአሸባሪዎች ጥቃት ሊፈጸም እንደሚችል አስተማማኝ መረጃ ደርሶኛል ያለችው አሜሪካ ከናይሮቢ ባሻገር በሌሎች የኬንያ የባህር ዳርቻ ከተሞች የአብራሪዎች ጥቃት እንደሚኖርም አሳስባለች።
የብሪታኒያ መንግስትም ባወጣው የጉዞ ማስጠንቀቂያ የብሪታኒያ ዜጎች ከሶማሊያና ኬንያ ድንበር አካባቢ እንዲርቁ እንዲሁም ከባህር ዳርቻዎች እንዳይንቀሳቀሱ አሳስበዋል።
በኬንያ ናይሮቢ ሞምባሳና ማሊንዲ የአሸባሪዎች ጥቃት ሊኖር እንደሚችል ያሳሰበው የብሪታኒያ መንግስት በዋናነት ናይሮቢ የስጋት ቀጠና መሆኗን ጨምሮ አመልክቷል።
የሁለት የምዕራብ መንግስታት የጉዞ ማስጠንቀቂያ የወጣው አልሻባብ በኬንያ ናይሮቢ በአንድ ዘመናዊ ሆቴል ላይ ጥቃት ከመፈጸሙ ከሳምንት በኋላ መሆኑን አልጀዚራ በዘገባው አስታውሷል።
ናይሮቢ ውስጥ በደረሰው በዚህ ጥቃት አንድ አሜሪካዊን ጨምሮ 21 ሰዎች መገደላቸውም ይታወሳል።