ታህሳስ ፳፭( ሃያ አምስት )ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የፕሬዚዳንት ሳልቫኪርና የተቃዋሚያቸው ሪክ ማቻር ወኪሎች ለድርድር አዲስ አበባ በሚገኙበት በዚህ ሰአት ፣ የአሜሪካ መንግስት የኢምባሲ ሰራተኞች በሙሉ አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ አዘዘ።
የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት እንዳስታወቀው ፣ የአሜሪካ የኢምባሲ ሰራተኞች በተዘጋጀላቸው አውሮፕላን ለቀው ይወጣሉ። ከጃንዋሪ 4 ጀምሮም ምንም አይነት አገልግሎት በኢምባሲው በኩል እንደማይሰጥ ግልጽ አድርጓል።
የመንግስት ታጣቂዎች በተቃዋሚዎች የተያዙትን ቦታዎች መልሰው ለመውሰድ በሚያደርጉት ጥረት ከፍተኛ ግጭት እና ምናልባትም የዘር ፍጅት ሊከሰት ይችላል ተብሎ ተሰግቷል።
የአሜሪካ መንግስት ለዜጎቹ የሰጠው መግለጫ በሰላም ድርድሩ ላይ ያለውን ተስፋ ቢያመነምነውም የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቴዎድሮስ አድሀኖም በሰጡት መግለጫ ግን ከሁለቱ ተደራዳሪዎች ጋር በተደረገው የተናጠል ድርድር የሰላም ጭላንጭል መታየቱን ገልጸዋል። የፊት ለፊት ንግግሩ ቅዳሜ እንደሚካሄድም አያይዘው ገልጸዋል።
በአገሪቱ ውስጥ በ10 ሺዎች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ያሉ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መንግስት እስካሁን ከ700 ያልበለጡ ዜጎችን ብቻ ማውጣቱ ታውቋል። አብዛኘው አገራት ዜጎቻቸውን በአየርና በመኪኖች አስወጥተዋል።