(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 9/2011) አሜሪካ በደቡብ ሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት እጃቸውን አስገብተዋል ያለቻቸውን የእስራኤል የጦር ጄኔራል ጨምሮ በሶስት ግለሰቦች ላይ ማዕቀብ ጣለች።
ሁለቱ የደቡብ ሱዳን ዜጎች መሆናቸውምታውቋል።
በደቡብ ሱዳን ግጭት ውስጥ እጃቸውን በማስገባትና ቀውሱን በማባባስ በሃገሪቱ ለተከሰተው ለ400 ሺህ ሰዎች ዕልቂት አስተዋጽኦ አድርገዋል የተባሉትን እስራኤላዊ ጡረተኛ ጄኔራል እስራኤል ዚቭ ሶስት ኩባንያዎች ላይም የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስቴር ማዕቀብ መጣሉን ኢየሩሳሌም ፖስት ዘግቧል።
እስራኤል ለደቡብ ሱዳን መንግስት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከሐምሌ 10/2011 ጀምሮ ዕውቅና የሰጠች ቢሆንም የደቡብ ሱዳን መንግስት በሃገሩ ለተቀጣጠለው ቀውስ እስራኤል ሰራሽ የጦር መሳሪያዎችና የስለላ ቁሳሶች ዕገዛ ማድረጋቸውን ሲገልጽ ቆይቷል።
ሆኖም የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስቴር የወጣውን ማዕቀብ በማስመልከት ባወጣው መረጃ መሳሪያዎቹ ከእስራኤል መንግስት ወደ ደቡብ ሱዳን የሚጓዙ ሳይሆኑ ጡረተኛው የእስራኤል ጄኔራል በልማት ዕቃ ስም የሚያሸጋግሩት መሆኑም ተጋልጧል።
የእስራኤል ጦር ሃይሎች አባልና የዘመቻ ዳይሬክተር የነበሩት ሜጀር ጄኔራል እስራኤል ዚቭ ጦርነቱ በደቡብ ሱዳን ከፈነዳበት እንደ አውሮፓውይናኡ አቆጣጠር ከ2013 ጀምሮ የእርሻና የቤት ግንባታ ቁሶችን ለደቡብ ሱዳን መንግስት የሚልክ በማስመሰል ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ሽያጭ ሲያከናውኑ መቆየታቸው ተገልጧል።
በዚህም የ150 ሚሊየን ዶላር የጦር መሳሪያ ሽያጭ ያካሄዱ ሲሆን ገንዘቡንም ከሃገሪቱ የነዳጅ ሽያጭ ሲወስዱ መቆየታቸው ተመልክቷል።
በደቡብ ሱዳን መንግስት ውስጥ ስልጣን ላይ ካሉ ባለስልጣናት ጋር የጥቅም ግንኙነት በመመስረትና ለነርሱ የጸጥታ ዋስትና በመስጠት የተካሄደው የጦር መሳሪያ ንግድ በዚያች ሃገር ለነበረው ቀውስ ሚናው የጎላ እንደነበርም ተጠቅሷል።
ጄኔራሉ በዚህም ሳይወሰኑ ቅጥረኞቹን በማሰማራት የደቡብ ሱዳን የነዳጅ ማውጫዎች ላይ ጥቃት በመፈጸም የራሳቸው ኩባንያ በጸጥታ ማስከበር ስራ ውስጥ እንዲገባና ገንዘብ እንዲከፈለው ያደርጉ እንደነበርም ይፋ ሆኗል።
በዚህና መሰል በደቡብ ሱዳን ውስጥ ለተፈጠረው ቀውስ ከፍተኛ ሚና አላቸው በተባሉት የቀድሞው የእስራኤል የጦር ከፍተኛ አዛዥ ሜጄር ጄኔራል እስራኤል ዚቭና ኩባንያዎቻቸው ላይ የአሜሪካ ገንዘብ ሚኒስቴር ማዕቀብ ጥሏል።
ግሎባል ኤን ቲ ኤም ሊሚትድ ግሎባል ሎው ኢንፎርስመንት ኤንድ ሴኩሪቲ ሊሚትድ እንዲሁም ግሎባል አይ ዜድ ግሩፕ ሊሚትድ የተባሉት የጄኔራሉ ኩባንያዎችም ላይ የአሜሪካ መንግስት ማዕቀብ ጥሏል።
ከጄኔራሉ በተጨማሪ የደቡብ ሱዳን ተወላጅ በሆኑ ኦባክ ዊልያም አለዋ በተባሉ ነጋዴና ግሪጎራ ቫዚሊ በተባሉ የደቡብ ሱዳን ሃገረ ገዢ ላይም ማዕቀብ መጣሉን ከእየሩሳሌም ፖስት ዘገባ መረዳት ተችሏል።