በሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው ላይ የተገኙ አዳዲስ መረጃዎች ይፋ ሆኑ

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 9/ 2011) መርማሪ ፖሊስ በሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው ላይ የተገኙ አዳዲስ ተሳትፎዎችን ይፋ አደረገ።

በቀድሞው የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው ላይ በምርመራ ወቅት ያገኛቸውን አዲስ የወንጀል ተሳትፎዎች ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል።

መርማሪ ፖሊስ እንደገለጸው ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው ከሕዳሴው ግድብ እና ከልዩ ልዩ ዓለምአቀፍና የሀገር ውስጥ ተቋማት ጋር ያደረጓቸው ውሎች እንዲሁም የተከፈሉ ገንዘቦች ሕገወጦች ናቸው።

ለሕዳሴው ግድብ ኤክትሮ ሚካኒካል ስራ ሚቴክ 25 በመቶ ሰርቶ 65 በመቶው 16 ቢሊየን ብር ከተከፈለው በኋላ 7 ቢሊየን ያህሉ በኦዲት የደረሰበትን ማረጋገጥ አልተቻለም ብሏል።

የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ሃይ-ቴክ ኢንዱስትሪ ሲ ኢ አይ ኢ ሲ ከተባለ የቻይና ኩባንያ ያለጨረታ፣ ያለዕቅድና የግዥ ፍላጎት በቁጥር 100 የሆኑ የእግረኛ ራዳሮች በ8 ሚሊየን 581 ሺህ 92 የአሜሪካ ዶላር የግዥ ውል ስምምነት እንዲፈጸም ተደርጓል።

ይሕንን ሕገ ውጥ ውል ታዲያ ያጸደቁት ሚጄር ጄናራል ክንፈ ዳኘው ናቸው።

            ሜቴክ ከሃይ ቴክ ኢንጅነሪንግ ኢንዱስትሪ ኤል አይ ቲ ከተባለ የቻይና ኩባንያ ያለጨረታ፣ ያለ እቅድና የግዥ ፍላጎት በቁጥር 100 የሆኑ የእግረኛ ራዳሮችን በ10 ሚሊየን 236 ሺህ 700 የአሜሪካ ዶላር  የግዥ ውል ስምምነት እንዲፈጸም እድርገዋልም ነው የተባለው።

ውሉን በማፅደቅ የተጠረጠሩ፣ 10 የእግረኛ ራዳሮችን ብቻ የተረከቡ መሆኑና የቀሩት 90 የእግረኛ ራዳሮች የት እንዳሉ የማይታወቅ መሆኑን ፖሊስ ጠቅሷል፤

በዚህም ከ18 ሚሊየን 817 ሺህ የአሜሪካ ዶላር በላይ የመንግስትና የህዝብ ሃብት ያለአግባብ አባክነዋል በሚል መጠርጣራቸውን ነው ፖሊስ የገለጸው።

ከህዳሴው ግድብ የኤሌክትሮ መካኒካልና የሃይድሮሊክ ስራዎችና የተርባይኖች ግዥን በተመለከተ ግለሰቡ የሜቴክ ዋና ዳይሬክተር በነበሩበት ወቅት ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን ጋር በፈረንጆቹ ጥቅምት ወር 2011 በተፈረመ የ24 ቢሊየን 400 ሚሊየን 463 ሺህ 424 ብር ከ96 ሳንቲም ውል ተፈራርመዋል።

            በዚህ ስራ ሜቴክ 23 በመቶ ብቻ አከናውኖ ሳለ የውሉን 65 ነጥብ 65 በመቶ ወይም 16 ቢሊየን 790 ሚሊየን 601 ሺህ 80 ብር ከ48 ሳንቲም ላላከናወነው ስራ ክፍያ እንዲፈጸም ተደርጓል።

            ከዚህ ገንዘብ ውስጥ 7 ቢሊየን 276 ሚሊየን 408 ሺህ 897 ብር ከ60 ሳንቲም ብር የት እንደደረሰ ወይም ለምን ስራ እንዳዋሉት አይታወቅም ሲል አስረድቷል ፖሊስ።

ለግድቡ የሚሆኑት አምስት ተርባይኖች ያለ ጨረታ ከውጭ ሃገር ያገለገሉ እና የታለመለትን ሃይል ማመንጨት የማይችሉ በተጋነነ ዋጋ እንዲገዙ በማድረግ በሃገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱም ነው የተገለጸው።

            ሜቴክ ስራውን እሰራለሁ ብሎ ከተረከበ በኋላ ከህግ ውጭ ስራውን ሌሎች ድርጅቶች በንዑስ ተቋራጭነት አላግባብ መስጠቱን፣ ለግድቡ የሚሆን ሲሚንቶ በመሰቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ እንዲቀርብ የተደረገበት አግባብ ከዋጋ፣ ከጥራትና ከቦታ ርቀት አንጻር አግባብ አለመሆኑ ፥ጥራቱ የወረደና ግድቡ ከሚያስፈልገው ሲሚንቶ በላይ እየቀረበ ብዙ ሺህ ኩንታል ሲሚንቶ እንዲበላሽ ሆኗል ተብሏል።

ከግድቡ ስራ ጋር በተያያዘ ሜቴክ የሚፈጽማቸው የትራንስፖርት አገልግሎት ግዥዎች ላይ በርካታ ወንጀሎች መፈጸማቸውንና ከዚህ ጋር የተያያዙ በርካታ ጥቆማዎችንም አቅርቧል።

ለቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ የተፈፀመ ኮንስትራክሽን ማሽነሪዎች እንዲሁም የመኪና ኢንጅኖችን በተመለከተ ግለሰቡ ሜቴክን በሚመሩበት ወቅት ለቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ ተብለው ከ2002 እስከ 2005 ዓ.ም ድረስ ከውጭ የተገዙ የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎች፣ የማሽን አካላትና የመኪና ኢንጅኖች ግዥ ሲፈጸም በህጉ መሰረት የግዥ ፍላጎት ቀርቦ ጨረታ አልወጣም።

            ከተለያዩ 13 አይነት ኩባንያዎች በጠቅላላው ከ29 በላይ ውሎች እንዲፈጸሙ በማድረግ ውሎችን በማፅደቅ በጠቅላላው ከ1 ቢሊየን ዶላር በላይ አለም አቀፍ ግዥ በመፈጸም መንግስት ከገበያ ውድድር ማግኘት የሚገባውን ጥቅም ማሳጣታቸውም ነው የተነገረው።

ሌበኸር ወርክ ጂ ኤም ቢ ኤች ከተባለ የጀርመን ኩባንያ 6 ሚሊየን 465 ሺህ ዩሮ የሚያወጡ 3 አዳዲስና 2 ያገለገሉ ተንቀሳቃሽ ክሬኖችን እንዲሁም ከዚሁ ኩባንያ እና ሃገር ውስጥ ከሚገኝ ቢዮ ፒ ኤል ሲ ከተባለ ኩባንያ ሌሎች ሶስት ክሬኖችና ኤሌክትሮድ በ6 ሚሊየን 997 ሺህ 65 ዩሮ ከአንድ አቅራቢ በተፈጸመ ግዥም ሜጄር ጄኔራል ክንፈ ተጠርጥረዋል።

የሜቴክ ሃላፊዎች ዳኑቢያን ኤርክራፍት ከተባለ የሃንጋሪ ኩባንያ ያለምንም ጨረታና ውድድር በቀጥታ ግዥ  የ660 ሺህ ዶላር የአገልግሎት ግዥ ፥ ፓወር ፕላስ ፒ ቲ ኢ ከተሰኘ የሲንጋፖር ኩባንያ የ56 ሚሊየን 943 ሺህ 800 የአሜሪካ ዶላር የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎች ግዥ የፈጸሙና መንግስት ከገበያ ውድድር ማግኘት ይችል የነበረውን የጥራትና የገንዘብ ጥቅም በማሳጣትም ተጠርጥረዋል።

            ቴክኖ ትሬድስ ኤስ አር ኤል ከተባለ የጣሊያን ኩባንያ የ4 ሚሊየን 540 ሺህ ዩሮ ያገለገሉ ክሬኖች ግዥ በመፈጸም መንግስት ማግኘት ይችል የነበረውን የጥራትና የገንዘብ ጥቅም በማሳጣትም እንዲሁ።

ችሎቱም በቀረቡት አዳዲስ የወንጀል ግኝቶችና መርማሪ ፖሊስ በጠየቀው የ14 ቀን ተጨማሪ የማጣሪያ ጊዜ ላይ የግራ ቀኙን ለማከራከር ለነገ ታህሳስ 9 ቀን 2011 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።