(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ17/2011) አመፅና የትጥቅ ትግል ኢትዮጵያን ስለሚያወድም በአሁኑ ጊዜ አስፈላጊ አይደለም ሲል የአርበኞች ግንቦት 7 ገለጸ።
የንቅናቄው ዋና ጸሃፊ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅቱ ከአመፅ ነፃ በሆነ በሰላማዊ መንገድ መታገልን ብቻ የሚጠይቅ ነው ብለዋል።
የአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ አመፅ እና ትጥቅን መሰረት ያደረገ ትግል ኢትዮጵያን ወደ ውድመት ከመምራት በስተቀር ሌላ ጥቅም የለውም ሲል ማብራሪያ ሰጥቷል።
ንቅናቄው ይሕንኑ በመረዳቱም አባላቱ በየትኛውም የአመፅ ድርጊት እንዳይሳተፉ ጥብቅ ማሳሰቢያ ማስተላለፉን የንቅናቄው ዋና ጸሃፊ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
አቶ አንዳርጋቸው እንዳሉት የአርበኞች ግንቦት 7 አብዛኛዎቹ ታጣቂዎቹ ትጥቅ ፈተዋል።
ታጣቂዎቹ ወደ ካምፕ እንዲገቡ መደረጉንም ነው ያስታወቁት። በኤርትራ የነበሩ ከ300 በላይ ታጣቂዎች እዛው ኤርትራ ትጥቃቸውን ፈተዋል።
በሃገር ውስጥ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ከ500 በላይ ታጣቂዎችም ትጥቅ ፈተው ወደ ካምፕ መግባታቸውንም ነው የተናገሩት።
አርበኞች ግንቦት 7 በየትኛውም አካባቢ እና ሁኔታ በስሙ ጥቃት የሚፈፅሙ አካላት ቢኖሩ ለመንግስት አሳልፎ እንደሚሰጥም ዋና ፀሃፊው አስታውቀዋል።
ግንባሩ ሰላማዊ የትግል አማራጭን ተቀብሎ ወደ ሀገር ቤት የገባው ኢትዮጵያን በመሰለ ሀገር በአመፅ የታገዘ የትጥቅ ትግል አዋጭ አለመሆኑን ስላመነ ነው ብለዋል ። አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ።
እኛ ኢትዮጵያውያን ሶርያ፣ የመን እና ሌሎች በአመፅ ከፈረሱ ሀገራት ልንማርም ይገባል ብለዋል።
የሀገሪቱን ሰላም ማስጠበቅ እና ህግን ማስከበር በዋናነት የመንግስት ሃላፊነት ሆኖ የፖለቲካ ድርጅቶችም ከአመፅ አባላቶቻቸውን በማራቅ መንግስትን ሊያግዙ ይገባል ሲሉ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል።