በአሜሪካ ወህኒ ቤት የ8 አመቱ ታዳጊ ሕይወቱ አለፈ

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 17/2011) በአሜሪካ ወህኒ ቤት የ8 አመቱ ታዳጊ ስደተኛ ትላንት ሕይወቱ ማለፉ ተሰማ።

በፈረንጆቹ የገና በአል ሕይወቱ ያለፈው የ8 አመቱ ታዳጊ የጓቲማላው ተወላጅ ፍሊፕ ጎሜዝ በዚህ ወር በአሜሪካ ወህኒ ቤት ሕይወታቸው ያለፈውን ታዳጊዎች ቁጥር ወደ 2 ከፍ አድርጎታል።

የታዳጊውን ሕልፈት ተከትሎ የአሜሪካ የጉምሩክና የድንበር ጥበቃ አሰራሩን በመከለስ አዲስ መመሪያ ተግባራዊ አድርጓል።

ሆስፒታል ቆይቶ ሲመለስ ህመሙ የተባባሰበት የ8 አመቱ ታዳጊ በአሜሪካ የድንበር ጠባቂዎች ከአባቱ ጋር የታሰረው በህገወጥ መንገድ አሜሪካ ገብታችኋል በሚል ነው።

ሕጻኑ ፍሊፕ አሎንዞ ጎሚዝ እሁድ እለት የህመም ምልክት እንደታየበት ያስተዋሉት የእስር ቤቱ ሃላፊዎች ወደ ሃኪም ቤት ወስደውታል።

ሃኪሞቹ በሕጻኑ ላይ የጉንፋን በኋላም የትኩሳት ምልክት ማግኘታቸውን ተከትሎ ለአንድ ሰአት ከ30 ደቂቃ ሆስፒታል ውስጥ ከቆዩ በኋላ አሞክስሊንና አይፕሮፊን መድሃኒት ሰጥተው እንዲሸኙት ከሲ ኤን ኤን ዘገባ መረዳት ተችሏል።

ሰኞ ምሽት የ8 አመቱ ታዳጊ በተደጋጋሚ ሲያስመልሰው ወደ ሆስፒታል በድጋሚ የተወሰደ ሲሆን ከሰአታት በኋላም ሕይወቱ ማለፉ ተመልክቷል።

የሕጻኑ ሞት መንስኤ ያልታወቀ ሲሆን ጉዳዩ ተመርምሮ ይፋ እንደሚደረግ የጉምሩክና የድንበር ጥበቃ ባለስልጣናቱ ይፋ አድርገዋል።

የአሜሪካ ጉምሩክና ድንበር ጥበቃ ኮሚሽነር ኤቪን ማክሌናን በሰጡት መግለጫ የታዳጊውን ፍሊፕ ጎሜዝን ሞት ተከትሎ የፖሊሲ ለውጥ መደረጉን አስታውቀዋል።

በሕገወጥ መንገድ ድንበር አቋርጠው በሚገኙት ልጆች በተለይም ከ10 አመት በታች በሆኑት ላይ ሁለተኛ ዙር የጤና ምርመራ ማድረግ እንዲሁም የሕክምና እርዳታ ከሚያደርጉ አካላት ጋር በትብብር መስራትና የቤተሰብ ማቆያ ስፍራዎችን ማመቻቸትን ጨምሮ ርምጃዎችን ለመውሰድ መዘጋጀቱን ገልጿል።

በዚህ በታህሳስ ወር መጀመሪያም የ7 አመት ታዳጊ ጓቲማላዊት በተመሳሳይ ሕይወቷ አልፏል።

የ7 አመቷ ጓቲማላዊት ጃክሊን ማክዊን ከአባቷ ጋር የ2000 ማይል ጉዞ አድርጋ በአሜሪካ ግዛት ኒው ሜክሲኮ ስትደርስ ከአባቷ ጋር ተይዛለች።

ታስራ 48 ሰአት ሳይሞላ ሕይወቷ ማለፉ ተሰምቷል።

በስደት ወደ አሜሪካ የሚገቡ ሰዎችን ለመቆጣጠር የትራምፕ አስተዳደር ያወጣውን ጥብቅ መመሪያ ተከትሎ የአሜሪካን ምድር የረገጡ ስደተኞች በብዛት ወደ ወሕኒ ማጋዙ ተጠናክሮ መቀጠሉ ይታወሳል።