ኢሳት (ሰኔ 2 ፥ 2008)
በሶማሊያ የሚንቀሳቀሰው አክራሪው የአልሻባብ ቡድን 43 የኢትዮጵያ ወታድሮችን መግደሉ ተነገረ። ግድያው የተፈጸመው የአልሻባብ የአጥፍቶ ጠፊዎች የወታደራዊ ሰፈር ዋናውን በር በመኪና ላይ በተጠመደ ፈንጅ በማጋየታቸው ሲሆን፣ ሟቾቹ የኢትዮጵያ ወታደሮች ለአፍሪካ ህብረት የሶማሊያ ሰላም አስከባሪ ሃይል (አሚሶም) ይሰሩ የነበሩ ናቸው ተብሏል።
ወታደራዊ ጥቃቱን የፈጸምነው እኛ ነን ሲል የአልሻባብ ወታደራዊ ተልዕኮዎች ቃል አቀባይ አብዲያሲስ አቡ ሙሳብ ለሮይተርስ መናገራቸው ተመልክቷል። ቃል አቀባዩ ከአልሻባብ ወገን በርካታ ወታደሮች መሞታቸው፣ ሆኖም የሟቾችንም ሆነ የቁስለኞችን ቁጥር ከመግለጽ ተቆጥበዋል።
በአቅራቢያ በሚገኘው ወታደራዊ ሰፈር በጅቡቲ ወታድሮች የተቃጣባቸውን ጥቃት መመከታቸውንም አብዲያሲስ አቡ ሙሳብ መናገራቸውን ሮይተርስ አመልክቷል።
ጥቃቱ የተፈጸመው ሃልጋን ተብላ በምትጠራው ከሞቃዲሾ 300 ኪሎሜትር በስተሰሜን በምትርቅ ወታደራዊ ሰፈር እንደሆነም ተመልክቷል።
ጥቃቱን ተከትሎ ከፍተኛ ፍንዳታ የተሰማ ሲሆን፣ የተኩስ ልውውጥ መደረጉም ታውቋል። ሃልጋን የሚገኘው ወታደራዊ ሰፈር እንደወደመ የአክራሪ ቡድኑ ቃል አቀባይ አክሎ ተናግሯል።
የዛሬውን ጥቃት አስመልክቶ በሶማሊያ የአፍሪካ ሰላም አስከባሪ ሃይል በሰጠው መግለጫ አሚሶም በአልሻባብ የተቃጣውን ጥቃት በመመከት 110 የልሻባብ አማጽያንን ገድያለሁ ብሏል። ድርጅቱ ብዛት ያለው መሳሪያም መማረኩን የአሚሶም ቃል አቀባይ ሌተናንት ኮሎኔል ጆ ክበት ለሮይተርስ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
አምስት ከፍተኛ የአልሻባብ አመራሮችን ጨምሮ 165 ታጣቂዎች መገደላቸውን ያስታወቀው መከላከልያ ሚኒስቴር በበኩሉ በኢትዮጵያ ወታደሮች በኩል ሰለደረሰ ጉዳት የሰጠው ዝርዝር መረጃ የለም። ሚኒስቴሩ ከተገልደሉት አምስት የአልሻባብ አመራሮች መካከል አንደኛው የሶማሊያ ዜግነት የሌለው እንደሆነ ቢገልጽም፣ የግለሰቡን ማንነንት ግን ሳይገልጽ ቀርቷል።
የኢትዮጵያ የኮሚውኒኬሽን ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው ከ100 በላይ የአልሻባብ ታጣቂዎች መገደላቸውንና የቀሩትም እየታደኑ ነው ሲሉ ለአሶሼይትድ ፕሬስ ተናግረዋል። ሆኖም ምን ያክል የኢትዮጵያ ወታደሮች እንደሞቱና እንደቆሰሉ የተናገሩት ነገር እንደሌለ የዜና ወኪሉ አስነብቧል።
አልሻባብ በአሚሶም ሃይል ላይ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ሲያደርስ እንደነበር ይታወቃል። ከወራት በፊት ቡድኑ በኬንያና ሶማሊያ ድንበር ኤል አዴ በተባለ ካምፕ በኬንያ ወታደሮች ላይ ባደረሰው ጥቃት 100 የሚሆኑ ወታደሮችን መግደሉ ይታወሳል። አልሻባብ በምዕራብያውያን የሚታገዘውን የሶማሊያን መንግስት ለመጣልና በሻሪያ የሚመራ መንግስት ለማቋቋም በባለስልጣናት፣ በአሚሶም ጸጥታ አስከባሪዎች እና የጸጥታ ሃይሎች ላይ የቦምብ እና የመሳሪያ ጥቃት እያደረሰ ያለ ድርጅት ነው።