አልሸባብ የኢትዮጵያ ጦር የያዘውን ከተማ መልሶ ያዘ

መጋቢት ፱ (ዘጠኝ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም 

ኢሳት ዜና:-ከኢትዮጵያ፣ ከኬንያ እና ከሶማሊያ መንግስት ወታደሮች ከፍተኛ ጥቃት ሲደርስበት የቆየው አልሸባብ፣ ትክክለኛ ምክንያቱ ባልተወቀ ሁኔታ የኢትዮጵያ ጦር ከባይደዋ አቅራቢያ የምትገኘዋን የሁድሩ ከተማን ለቆ መውጣቱን ተከትሎ፣ ከተማዋን መልሶ ተቆጣጥሯል። የከተማዋ ነዋሪዎች አልሸባብ አካባቢውን ለረጅም ጊዜ ከቦ መቀመጡ የምግብ እጥረት እንዲፈጠር ማድረጉን በምሬት ሲናገሩ መደመጣቸውን ጋሮየ ኦን ላይ ገልጿል።

የኢትዮጵያ መንግስት ጦር ከተማዋን ለቆ ስለወጣበት ምክንያት የተገለጸ ነገር የለም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በሞቃዲሾ በደረሰ ፍንዳታ 8 ሰዎች ሲገደሉ ፣ ከ20 ያላነሱ ሰዎች ቆስለዋል። ጉዳቱ የደረሰው አንድ አጥፍቶ ጠፊ በፕሬዚዳንቱ ቤተመንግስት አቅራቢያ አንድ መኪና በማጋየቱ ነው። የፈሪዎች ድርጊት በማለት ድርጊቱን ያወገዙት ጠቅላይ ሚ/ር አብዲ ፋራህ፣ አልሸባብን ተጠያቄ አድርገዋል። በድርጊቱ የአገሪቱ የጸጥታ ሹም መቁሰላቸው ታውቋል።